በአዲስ አበባ በአንድ ቢሊየን ብር ወጪ የተገነቡ 51 የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ

64

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሰኔ 5/2013 በአዲስ አበባ ከተማ በአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ 51 የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የተለያዩ የስፖርት ቤተሰቦች በተገኙበት የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎቹ ተመርቀዋል።

በዛሬው እለት ከተመረቁ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች መካከል ፈረንሳይ ለጋሲዮን የሚገኘው ጨፌ ሜዳ ማዘውተሪያ ፣ የአፍንጮ በር ሁለገብ ሜዳ፣ የራስ ኃይሉ ዓለም ዓቀፍ የውሃ መዋኛ ገንዳ ይገኙበታል።

ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ የእግር ኳስ ሜዳዎች፣ ሦስት በአንድና ሁለት በአንድ የሆኑ የእጅ ኳስ፣ የቅርጫት ኳስና መረብ ኳስ ሜዳዎች ይገኙበታል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፤ የከተማ አስተዳደሩ በ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት የወጣቶችና የስፖርት ቤተሰቡ ለረጅም ጊዜ የሚያቀርቡትን ጥያቄዎች መፍትሔ ለመስጠት ሲሰራ እንደነበር ተናግረዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ለወጣቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት የስፖርት ማዘውተሪያ ለመገንባት ቁርጠኛ መሆኑን  በዛሬው እለት የተመረቁት 51 የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች  ጥሩ ማሳያዎች ናቸው ብለዋል።

በቀጣይም  የስፖርት ቤተሰቡንና የወጣቶችን የስፖርት ልማት ፕሮጀክቶችን ጥያቄዎች ለመመለስ ግንባታዎችን በፍጥነት ጀምሮ በፍጥነት ለማጠናቀቅ ከተማ አስተዳደሩ የሚችለውን ያደርጋል ሲሉም ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም