ለመተከል ተፈናቃዮች የሚውል የቤት ክዳን ቆርቆሮና የሚስማር ድጋፍ ተደረገ

98

ሰኔ 4/2013 (ኢዜአ) ለመተከል ተፈናቃይ ዜጎች መልሶ ማቋቋም የሚውል የቤት ክዳን ቆርቆሮና የሚስማር ድጋፍ ተደረገ።

ድጋፉን ያደረጉት የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባዔ እና የመተከልና አካባቢው ተፈናቃዮች ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ናቸው።

በመተከል ዞን የተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደቀያቸው መልሶ ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ማህበራቱ በአገር ውስጥና በውጭ ከሚኖሩ ለጋሽ ዜጎች ባገኙት ገንዘብ በድምሩ 884 ሺህ ብር የሚገመት የቤት ክዳን ቆርቆሮና ሚስማር ድጋፍ ተደርጓል።

የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባዔ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ዳዊት መኮንን፤ ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ወደነበሩበት ቦታ እንዲመለሱ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

የተደረገው ድጋፍ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ሌሎች አጋዥ ድርጅቶችና አካላት ጭምር ድጋፍ እንዲያደርጉ መነሳሳትን ለመፍጠር እንደሆነም ተናግረዋል።

የመተከልና አካባቢው ተፈናቃዮች አስተባባሪ ግብረ ኃይል ሰብሳቢ ዶክተር አያሌው አባተ፤ ኮሚቴው ከዚህ ቀደም ለተፈናቃይ ወገኖች የሚውል ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የዱቄት፣ የንጽህና መጠበቂያ ሳሙና እና የጨው ድጋፍ ስለማድረጉ አስታውሰዋል።

አሁንም በዞኑ የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም ተከትሎ መንግሥት ተፈናቃይ ዜጎችን ወደነበሩበት ለመመለስ እያደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ በአገር ውስጥና በውጭ ከሚኖሩ ዜጎች የተገኘ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።

የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረኃይል ኮማንድ ፖስት ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል አሥራት ዴኔሮ፤ ተፈናቃይ ወገኖች ወደነበሩበት ቀዬ ሲመለሱ የአገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላት ደህንነታቸውን ለመጠበቅና ስጋታቸውን ለማስወገድ ከእነርሱ ጋር እንደሚሆን አረጋግጠዋል።

በዞኑ ያለው የጸጥታ ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱን ተከትሎ ተፈናቃይ ወገኖችን ወደቀያቸው ለመመለስ የሚደረገውን ሥራ ለማገዝ የተለያዩ ተቋማት፣ ግለሰቦች፣ የአማራ እና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የተለያዩ ድጋፎችን እያደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል።

ባለጸጎቹ አቶ በላይነህ ክንዴ፣ አቶ ወርቁ አይተነው፣ የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባዔ እና የመተከልና አካባቢው ተፈናቃዮች አስተባባሪ ግብረ ኃይል እያደረጉት ያለው የቆርቆሮ፣ የድንኳን፣ የሚስማርና ሌሎችም ምግብና ምግብ-ነክ ያልሆኑ ድጋፎች ደስታን የሚፈጥርና እፎይታንም የሚሰጥ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ፤ ተፈናቃይ ወገኖች ወደነበሩበት ቀዬ ሲመለሱ ሳይቸገሩ ሰብአዊ ድጋፍ የሚያገኙበት ሁኔታ እየተመቻቸ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

መንግሥት ተፈናቃይ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን ማንኛውም ድርጅትና ግለሰብ የአርሶ አደር የእርሻ መሳሪያን ጨምሮ የሚችለውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማቋቋምና ወደ መደበኛ ህይወታቸው ለመመለስ መንግሥት ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ ሌሎች አካላትም ወገኖቻቸውን በመርዳት የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ ጥሪ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም