በኦሮሚያ ክልል አምስት ከተሞች የወጣቶች ማዕከላትን የማደራጀት ስራ ተከነወነ

84

አዳማ ፤ሰኔ 04/2013 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል አምስት ከተሞች የወጣቶች ማዕከላትን ወደ ሳይንስ ካፌ ለመቀየር የማደራጀት ስራ በማከናወን አገልግሎት እንዲጀምሩ መደረጉን የኦሮሚያ ሳይንስ ቴክኖሎጂና መረጃ ግንኙነት ባለስልጣን ገለጸ።
ባለስልጣኑ በአዳማ ከተማ የሳይንስ ካፌ አስመርቋል።
በምረቃው ስነ-ስርዓት የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጅማ ቱሉ እንዳሉት፤ በክልሉ አዲሱን ትውልድ በሳይንስና ቴክኖሎጂ  እራሱን እንዲያበቃ ለማስቻል እየተሰራ ነው።
እስካሁንም  በ40 ሚሊዮን ብር በጀት በአዳማ፣ ሻሻመኔና ባሌ ሮቤን ጨምሮ በክልሉ የተለያዩ አምስት ከተሞች የወጣቶች ማዕከላትን ወደ ሳይንስ ካፌ ለመቀየር በአይሲቲ የማደራጀት ስራ  በማከናወን አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን  ገልጸዋል።

በአዳማ ከተማ ትናንት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የሳይንስ ካፌ የሁለተኛና አንደኛ ደረጃ ተማሪዎች፣ ጥናትና ምርምር የሚሰሩ ወጣቶች ለግብዓት የሚጠቀሙበት ነው ብለዋል።
በባለስልጣኑ የጥራት መሰረተ ልማት ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ፈይሣ በበኩላቸው፣  ባለስልጣኑ የሳይንስ ካፌዎች  ከ500ሺህ በላይ መጽሐፍት የያዙ ዲጂታል ቤተመጽሐፍት እንዳሉት ተናግረዋል።
በተጨማሪም 19 የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የያዙ ሶፍትዌሮች በማበልጸግ ወደ አገልግሎት ማስገባታቸውን ገልጸዋል።
በምረቃው ስነ-ሰርዓት የተገኙት የሳይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር ተወካይ  ሰላምይሁን አደፍርስ እንደገለጹት፤ መስሪያ ቤታቸው  በክልሉ ለተደራጁ የሳይንስ ካፌዎች ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ በዓይነትና ገንዘበ  ድጋፍ አድርጓል።

ይህም  በቀጣይ ሳይንቲስቶችንና ተመራማሪዎች በብዛት ለማፍራት የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ጭምር መሰረት ለመጣል መሆኑን አስረድተዋል።
የከተማዋ  ወጣት  በሳይንሳዊ ክህሎትና ቴክኖሎጂ  ለማነፅ የሳይንስ ካፌው ሚና የላቀ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የአዳማ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሙሐመድ ጉዬ ናቸው።
የክልሉ መንግስት እንዲሁም የሳይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር  የሳይንስ ካፌውን ለማደራጀት ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም