በባህርዳር ከተማ የ4 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የአስፓልት ኮንክሪት መንገዶች ግንባታ ተጀመረ

114

ባህርዳር ሰኔ 03/2013 (ኢዜአ)- በባህርዳር ከተማ በ400 ሚሊየን ብር የ4 ነጥብ 5 ኪሎ ሜርት የአስፓልት ኮንክሪት መንገዶችን ግንባታ ተጀመረ።
በከተማው በአጼ ቴዎድሮስና በአጼ ሚኒሊክ ክፍለ ከተሞች የሁለት መንገዶች ግንባታ ማስጀመሪያ ስነ ስርአት ዛሬ ተካሂዷል።

የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ የመንገዱን ግንባታ አስጀምረዋል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በወቅቱ እንዳሉት አስተዳደሩ የከተማው ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ያነሷቸው የነበሩ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት  እየሰራ ነው።

"ግንባታቸው የተጀመረ የመንገዶችም የዚሁ ማሳያ ናቸው" ብለዋል ።

በአጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ ከዳያስፖራ አስፓልት እስከ ዘንዘልማ አስፋልትያለው 30 ሜትርስፋትያለው የ3 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ በይፋ መጀመሩን አብስረዋል ።

የመንገዱ ግንባታ ለአማራ መንገድ ስራዎች ድርጅት ባለስልጣን መሰጠቱንና በሁለት ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።

በሚኒሊክ ክፍለ ከተማም በተለምዶ ልደታ በሚባል አካባቢ የአንድ ኪሎ ሜትር አስፓልት መንገድ  በቻይና ኩባንያ የሚገነባ መሆኑን ይፋ አድርገዋል።

የአስፓልት መንገዶቹ መገንባት የከተማውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከማፋጠን ባሻገር ገጽታውን ለማሻሻል እንደሚያስችል ገልጸዋል።

የአጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተዋበ አንለይ እንዳሉት "የሚገነባው መንገድ የዳያስፖራ፣ የኪዳነ ምህረትና የማራኪ አካባቢ ነዋሪዎችን ችግር ይፈታል" ብለዋል።

የአስፓልት መንገድ ግንባታው ቤት ገንብተው ያጠናቀቁ እንዲገቡና ግንባታ ያልጀመሩ እንዲጀምሩ የሚያስችል በመሆኑ ለአካባቢው እድገት መፋጠን ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የደብረ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምህረት አስተዳዳሪ መላከ ገነት ዮሃንስ ጥሩህ በአካባቢው ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ መኖራቸውን በመግለጽ "አስፓልት መንገድ ባለመኖሩ  በበጋ በአቧራ፣ በክረምት ደግሞ በጭቃ ስንቸገር ቆይተናል" ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ የመንገዱን ግንባታ ማስጀመሩ እንዳስደሰታቸው ጠቁመው መንገዱ ግንባታው በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ የአካባቢውን ነዋሪዎች በማስተባበር አስፈላጊውን ጥረት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም