ሀገራዊ የባህል እሴቶች ሳይበረዙ ለትውልድ እንዲተላለፉ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ

178
ደብረ ማርቆሰ ግንቦት 7/2010 ዩኒቨርሲቲዎች ሀገራዊ የባህል እሴቶች ሳይበረዙ ለተተኪው ትውልድ እንዲተላለፉ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተጠቆመ። ስድስተኛው የሀዲስ አለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ዓመታዊ አውደጥናት "ባህልና ስነምግባር በኢትዮጵያ ከየት ወደ የት" በሚል ጽንስ ሀሳብ በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ታፈረ መላኩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ባህልን ጠብቆና ተንከባክቦ መያዝ ከተቻለ የማንነት ማሳያ ከመሆን ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ፋይደም ይኖረዋል። በመሆኑም ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች አገራዊ የባህል እሴቶች ሳይከለሱና ሳይበረዙ ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ በሚደረጉ ጥረቶች የበኩላቸውን እገዛ በማድረግ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል። "በተለይ የህዝቦች የመቻቻልና የአብሮነት ግንኙነት ከፍ ወዳለ ደረጃ እንዲሰርስ አተኩረው መስራት ይኖርባቸዋል" ብለዋል። ዩኒቨርሲቲው ያዘጋጀው አውደ ጥናት በሀዝቦች መካከል ለዘመናት አብሮ የቆየውን የመቻቻልና የመተሳሰብ ባህል በአሁኑ ወቅት እየገጠመ ካለው ማንነትን ከሚያጠፋ ተግባር መከላከል የሚቻልበትን ግንዛቤ የማሳደግ ዓላማ አለው። ዶክተር ታፈረ እንዳሉት የአባቶች የመከባበር፣ የመቻቻልና የመተሳሰብ ባህል በአሁኑ ትውልድ እየተዘነጉ በመምጣታቸው ወጣቱ ባህሉን በአግባቡ አውቆ ለቀጣይ ትውልድ የሚያስተላልፍበት መንገድ ሊጠናከር ይገባል። በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ሲስተር ገነት ደጉ በበኩላቸው የሀዲስ አለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ባለፉት 6 ዓመታት ለታሪክ ተመራማሪዎች መረጃ የሚሆኑ ጹህፎችን በማሰባሰብና ለባህል ትስስር መጠናከር ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ተተኪ የኪነጥበብ ሰዎች ለማፍራት ስልጠናዎችን የመስጠትና የጠፉና የተዘነጉ የማህበረሰቡ ወግና ልማዶች ከአለባበስ ጀምሮ እስከ ባህላዊ ዳኝነት እንዲታወሱ የማድረግ ተግባር ማከናወኑንም ተናግረዋል። ከተሳታፊዎች መካከል የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ አበረ አዳሙ እንዳሉት የሀዲስ አለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም በየዓመቱ አውደጥናቶች ያዘጋጃል። አውደጥናቱም ባህልና ኪነጥበብ ያሉበትን ደረጃ የበለጠ እንዲፈተሽና በዘርፉ የሚስተዋለውን ክፍተት ለማስተካከል ምሁራን የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን አመልክተዋል። "ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወጣቱ የኢትዮጵያዊነት ባህል አሴቱን ዘንግቶ ታላላቆቹን ካለማክበር ባለፈ በሀገር ሀብትና ንብረት ላይ ግዴለሽ እየሆነ መጥቷል" ሲሉም ገልጸዋል። ይህን ለማስተካከል የሃይማኖት አባቶች፣ ወላጆች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የትምህርት ተቋማትና መንግስት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል። ከአዲስ አበባ የመጡት አቶ ደሰለኝ ስዩም በበኩላቸው "ከባህል ጋር ተያይዘው የሚቀርቡ ጥናቶች እራሳችንን እንድንፈትሽ ከማድረግ ባለፈ ኃላፊነትን ለመውሰድ የሚያነሳሱ በመሆናቸው ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል" ብለዋል። ባለፉት ሁለት ቀናት በዩኒቨርሲቲው በተካሄደው አውደ ጥናቱ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ጥናት አቅራቢዎች፣ የኪነ ጥብብ ሰዎችና ሌሎች ምሁራን የተሳተፉ ሲሆኑ አሥር የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎችም ቀርበው ማጎልበቻ ሀሳብ ተሰጥቶባቸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም