"አባጅፋር ለመፎ" የተሰኘ ሙዚቃዊ ትያትር ለእይታ ቀረበ

157

ጅማ፣ ግንቦት 29/2013 (ኢዜአ) በጅማ ዩኒቨርሲቲ አምፊ ትያትር "አባጅፋር ለመፎ" የተሰኘ ሙዚቃዊ ቲያትር ለእይታ ቀረበ፡፡

ሙዚቃዊ ትያትሩ አንድነትንና የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በመነጋገር መፍታት መማር የሚቻልበት አጋጣሚ መኖሩን ከታሪክ የሚያስረዳ ጭብጥ የያዘ መሆኑ ተመላክቷል።

የትያትሩ ደራሲና አዘጋጅ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ቲያትርና ጥበባት መምህር ዘላለም ተፈሪ ለኢዜአ እንደገለጹት ትያትሩ የአንድ ሰዓት ተኩል ርዝመት ያለው አስተማሪ ሙዚቃዊ ትያትር ነው፡፡

አዘጋጅና ደራሲው እንደገለጹት "አባ ጅፋር ለ54 አመታት ሲያስተዳድሩ ጦርነት ውስጥ የገቡበት ጊዜ አልነበረም፤ ይህም የሆነው ንጉሱ የሚፈጠሩ ችግሮችን ተነጋገሮ በመፍታት ያምኑ ስለነበር ነው" ብለዋል፡፡

የትያትሩ ጭብጥ ከታሪክ መማርንና ነገን የተሻለ ሰላማዊ ሀገር መፍጠር የሚያስችል ቁም ነገር ላይ የሚያጠነጥን መሆኑን ደራሲው ተናግረዋል፡፡

ትያትሩን ለማዘጋጀትና ለመለማመድ አንድ አመት ከሶስት ወር መፍጀቱን የገለጹት አዘጋጁ በየከተሞችና በዩኒቨርሲቲዎች መታየት ያለበት ስራ እንደሆነ ተናግሯል፡፡

የሙዚቃዊ ትያትሩ ረዳት አዘጋጅ ሴና አብራሃ "የሙዚቃ ትምህርት ክፍል፣ የቪዥዋልና የትያትር ተማሪዎች በመተባበር ጥሩ ስራ መስራት ችለናል" ብላለች፡፡

የሶስተኛ አመት የትያትር ተማሪ ሚደግሳ ደሳለኝ የኣባ ጅፋርን ገጸ ባህርይ ወክሎ ተጫውቷል፡፡

"ትያትሩ ታሪካዊ መልእክት ያለው በመሆኑ በጥንቃቄ ሰርተነዋል፤ ተወዶልናልም፤ ለወደፊትም ትያትሩን በስፋት ለማሳየትና በተጨማሪም ሌሎች ስራዎችን ለመስራት አበረታች ምላሽ ነበረው" ብሏል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ጀማል አባ ፊጣ በቀረበው ትያትር መደመማቸውን ተናግረዉ ’’ያልተነካ እምቅ ሀብት እንዳለን ተረድተናል’’ ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የሚችለውን ሁሉ ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ ’’ይህንን የተለየ አስተማሪ ትያትር የአካባቢያችንም ሆነ የሀገራችን ትያትር አድናቂ ሊያየው ያስፈልጋል’’ ሲሉም አመልክተዋል፡፡

"በተለይም በሁለት ቋንቋ መሰራቱና በአካባቢ ታሪክ ላይ መመስረቱ ሙዚቃዊ ትያትሩን የተለየ ያደርገዋል"  በማለት አድናቆታቸውን ችረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም