በምርጫው ሂደት የሳይበር ጥቃት እንዳያጋጥም በልዩ ትኩረት እየሰራን ነው- ኤጀንሲው

92

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27/2013 /ኢዜአ/ በምርጫው ሂደት የሳይበር ጥቃት እንዳያጋጥም በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ገለጸ።

የምርጫ የሳይበር ደህንነት ሁኔታ ማረጋገጥ ማለት ምርጫንና የምርጫን መሠረተ-ልማቶች ከሳይበር ሥጋት ወይም ጥቃት መጠበቅ ማለት ነው።

መረጃ ሰርሳሪዎች ይህም የምርጫ ጣቢያዎችን የምርጫ ማሽነሪዎች፣ የምርጫ ቁሳቁስ፣ የምርጫ ጽህፈት ቤት በይነ-መረብና መሠረተ ልማቶች እንዲሁም የመራጮች መረጃ ቋትን እንዳይበረበሩ፣ ሰርገው እንዳይገቡ ወይም ጉዳት እንዳይደርሱ መከላከል ነው፡፡

ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚካሄድ ይታወቃል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ከሚያስፈጽምባቸው ግብአቶች አንዱ የሚጠቀምባቸው ቴክኖሎጂዎችና የአሰራር ሥርዓቶች (ሲስተምስ) መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም የምርጫ ባለድርሻ አካላት የሳይበር ምህዳር አጠቃቀማቸው ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

በምርጫ ሂደቱ ቴክኖሎጂዎችና አሰራሮቹ ለሳይበር ጥቃት እንዳይጋለጡ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ድጋፍና ክትትል እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ለሳይበር ጥቃት ቢጋለጡና ሀገርና ህዝብን በእጂጉ ሊጎዱ የሚችሉ ተቋማትን በመለየት ኤጀንሲው በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ከነዚህ ተቋማት አንዱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ምርጫ ቦርድ መሆኑንም ዶክተር ሹመቴ  ገልጸዋል።

ዕጩ ተወዳዳሪዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ከምርጫው ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚገናኙ ተቋማት የሳይበር ጥቃት ኢላማ ሊሆኑ ስለሚችሉ እንዲጠነቀቁም መክረዋል።

መረጃ ሰርሳሪዎች ሐሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨትና መረጃ የማዛባት፤ መረጃን የማመሰቃቀል (ሀኪንግ)  ተግባር ሊያከናውኑ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።

የምርጫ ባለድርሻ አካላቱ ‘’ጥቃት ደርሶብናል’’ አለይም መረጃቸውን ማንቀሳቀስ ካልቻሉ ለኤጀንሲው በማሳወቅ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያገኙ ዶክተር ሹመቴ አረጋግጠዋል።

ኤጀንሲው ቁልፍ በሆኑ አገራዊ መሰረተ ልማቶች ጥቃት እንዳይደርስ የሚከላከል ቡድን ማቋቋሙን ጠቅሰዋል።

ቡድኑ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ወቅትና በድህረ ምርጫ ወቅቶች ሊያጋጥሙ የሚችሉ የሳይበር ጥቃቶችን ለመከላከል ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል።

ኤጀንሲው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሳይበር ደህንነት ጋር በተያያዘ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።


በምርጫ ወቅት ሰርሳሪዎች የሳይበር ምህዳሩን ተጠቅመው ጥቃት ሊያደርሱ እንደሚችሉ በመገንዘብ ከግለሰብ እስከ ተቋም ያሉ ባለድርሻ አካላት ሁሉ በጥንቃቄና በኃላፊነት እንዲሰሩም ዋና ዳይሬክተሩ መክረዋል።

አገሮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚካሄዱ አገራዊና ክልላዊ ምርጫዎች ላይ ዋነኛ ስጋት አንዱ የሳይበር ጥቃት እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኤሌክትሮኒክስ ድምፅ /Electronic voting/ የኤሌክትሮኒክ መሳሪያዎችን በመጠቀም ድምጽ መስጠትንና መቁጠርን የሚያግዝ ሥርዓት ሲሆን፣ እነዚህ የኤሌክትሮኒክ ድምጽ መስጫ ማሽኖች ደግሞ ከበይነ-መረብ ጋር የተገናኙ ኮምፒተሮችን ይጠቀማሉ።

የድምጽ መስጫ ማሽኖች ከበይነ-መረብ ጋር የተቆራኙ መሆናቸውን ተከትሎ የሳይበር ጥቃት ሰለባ ስለመሆናቸው መስማት እየተለመደ መጥቷል።

የአሜሪካን የ2016 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫን ጨምሮ በተለያዩ አገሮች ከምርጫ ጋር በተገናኘ የተለያዩ የሳይበር ጥቃቶች ተፈፅመዋል።

የሳይበር ጥቃቶችን በምርጫዎች ላይ የሚያደርሱ አካላት መነሻ ዓላማ በምርጫ ሂደቱ ወይም በውጤቱ ላይ ተጽዕኖ ማሳረፍ፤ ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደትን ተዓማኒነትና የህዝብን አመኔታ ማሳጣት ወይም ፖለቲካዊ አለመረጋጋት መፍጠር ነው።

የምርጫ ባለድርሻ አካላት በምርጫ ወቅት ማናቸውም ዓይነት የሳይበር ጥቃቶች እንዳይፈጸሙና የጥቃት ሰለባ እንዳይሆኑ ዘርፉን የሚመሩ የሙያተኛ ቡድን አባላትን በማደራጀት ጥንቃቄ ሊያደርጉና ግንዛቤ የማሳደግ ሥራዎች ሊሠሩ እንደሚገባ የሳይበር ደህንነት ባለሙያዎች ይመክራሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም