የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በምርጫ ላይ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማቅረብ የዜጎችን ንቃተ ህሊና ማሳደግ ይገባቸዋል--ዴኤታ ዶክተር ሙሉ ነጋ

68

ደብረብርሃን ፤ ግንቦት 25/ 2013(ኢዜአ) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በምርጫ ላይ  የጥናትና ምርምር  ስራዎችን  በማቅረብ የዜጎችን ንቃተ ህሊና ማሳደግ እንደሚገባቸው ተገለጸ።

ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ  "የዜጎች፣ የሲቪክ ማህበራትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ለሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ"  በሚል መሪ ሃሳብ  ያዘጋጀው የውይይት መድረክ ዛሬ ተካሄዷል።

በመድረኩ የተገኙት  የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር  ሙሉ  ነጋ  እንዳሉት  ፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በምርጫ ላይ  የጥናትና ምርምር  ስራዎችን  በማቅረብ የዜጎችን ንቃተ ህሊና ማሳደግ አለባቸው።

በጥናታዊ ጽሁፎች ላይ ተመስርቶ የሚካሄዱ የሀሳብ ፍጭቶች ፣ውይይቶችንና የሚሰጡ ትንታኔዎችን በመገናኛ ብዙሃን በማቅረብ ህዝቡ የሚበጀውን ፓርቲ በነጻነት እንዲመርጥ ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና በህዝብ ዘንድ ተአማኒ እንዲሆን የምሁራንና የሲቪክ ማህበራት ሳይንሳዊ ሃሳብ በማፍለቅ የህብረተሰቡን ንቃተ  ህሊና  ለማዳበር   የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።

የተዘጋጀው የውይይት መድረክም የሲቪክ ማህበራትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በምርጫው ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ሀገር ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማሻገር የተያዘውን ግብ ለማሳካት እንዲያግዝ ለማስቻል  ነው ሲሉ ተናግረዋል።

 የደብረብርሀን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ንጉስ ታደሰ በበኩላቸው፤ ምርጫ ዜጎች ሉአላዊ የስልጣን ባለቤትነታቸውን የሚያረጋግጡበት መድረክ  መሆኑን ገልጸዋል።

ህዝቡ በእውቀት ላይ የተመሰረተ የምርጫ ተሳትፎ  በማድረግ ለዴሞክራሲያዊ  ስርዓት  ግንባታው መሰረት እንዲጥል ሳይንሳዊና የዓለም ተሞክሮን ከግምት ውስጥ ያስገባ ሃሳብ በማመንጨት ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲያቸው ተከታታይ አውደ ጥናቶችን በማካሄድ መጪው ምርጫ  ሰላማዊ ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሀዊ ሆኖ እንዲሳካ ድርሻውን እየተወጣ መሆኑን አስረድተዋል።

የዛሬው መድረከም  በምርጫው ሂደት ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን በማስቀረት የተረጋጋች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የድርሻችንን ለማበርከት ታስቦ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የህዝብ አብሮነት፣ እኩልነትና አነድነትን ለማስፈን የፖለቲካ ፓርቲዎች በትብብር መስራት እንዳለባቸው ለማስገንዘብ ጭምር መሆኑን አመላክተዋል።

በመድረኩ ከ20 በላይ  የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች፣ ምሁራንና የሲቪክ ማህበራት መገኘታቸውን ኢዜአ ከደብረ ብርሃን ዘግቧል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም