በትግራይ የምህረት አዋጁ የሚመለከታቸው 56 የክስ መዝገቦች ተቋረጡ

50
መቀሌ ሀምሌ 27/2010 የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታን ለማሳደግና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በቅርቡ የጸደቀውን የምህረት አዋጅ ተከትሎ የ56 የክስ መዝገቦች እንዲቋረጥ መደረጉን የትግራይ ክልል ፍትህ ቢሮ አስታወቀ፡፡ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አረጋይ ገብረእግዚአብሄር ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በቅርቡ በአገር አቀፍ ደረጃ የጸደቀውን የምህረት አዋጅ በክልሉ ተግባራዊ ማድረግ ተጀምሯል። በእዚህም የምህረት አዋጁ የሚመለከታቸው 56 የክስ መዝገቦች ተቋርጠው ተከሳሾች ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጉን አመልክተዋል፡፡ ካለፈው ግንቦት 30ቀን 2010 ዓ.ም በፊት የፖለቲካ መብታቸውን ተግባራዊ ለማድረግ በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች የተሳተፉ ሰዎች ተጠያቂነታቸው ተነስቶ በምህረት ወደ ህብተሰቡ እንዲቀላቀሉ በአዋጁ በተደነገገው መሰረት የክስ መዝገቦቹ መቋረጣቸውን አስረድተዋል። እንደ አቶ አረጋይ ገለጻ በቅርቡ ወጥቶ ተግባራዊ የሆነው የምህረት አዋጁ የአገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር ለማስፋት የራሱ አስተዋጽኦ አለው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም