የኢትዮ ጅቡቲን ግንኙነት ለማጠናከር ተጨባጭ እርምጃዎች ይወሰዳሉ - የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር

63
ሚያዝያ 21/2010 የኢትዮጵያንና ጅቡቲን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ለማጠናከር ተጨባጭ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ምኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ተናገሩ፡፡ ዶክተር አቢይ አህመድ የመጀመሪያውን የውጭ ሀገር የስራ ጉብኝት በጂቡቲ ጀምረዋል፡፡ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች   የሁለትዮሽ ጉዳዮችን ጨምሮ፣ በክልላዊና አህጉራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡ በውይይታቸውም የወደብ፣ የመንገድና እርሻ ልማትን ጨምሮ የሁለቱን ሀገራት ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል፡፡ የጂቡቲው ፕሬዝዳንት እስማዔል ኡመር ጉሌህም ኢኮኖሚያዊ ውህደቱን ለማፋጠን ከአዲሱ አመራር ጋር በትብብር እንደሚሰሩ ገልጸው ለዚህም የፖሊሲ ማጣጣም ስራዎች እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ የሁለቱ ሀገራት ውጭ ጉዳይና የኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትሮችን ጨምሮ  መሰል ተቋማትን ያቀፈ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ተቋቁሞ በጉዳዩ ላይ ዝርዝር ሃሳብ እንዲቀርብም ፕሬዝዳንቱ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በጂቡቲ ፓርላማ ተገኝተውም ንግግር አድርገዋል፡፡ ለሀገሪቱ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  ባደረጉት ንግግር እንዳሉት የሁለቱ ሀገራት ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶችና  የምክር ቤት አባላት የሁለቱን ሀገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከር ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ የሁለቱ ሀገራት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች የእርስ በእርስ ግንኙነት ዴሞክራሲን ለማጎልበት ያበረከተውን አስተዋጽኦም አድንቀዋል፡፡ በኢጋድ የእርስ በእርስ የፓርላማ ግንኙነትም የሁለቱ ሀገራት ፓርላማዎች የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ነው ያብራሩት፡፡ ለኢኮኖሚያዊ ውህደቱ የተጣለው የመሰረት ድንጋይ ለፍሬ እንዲበቃ የሁለቱ ሀገራት ህግ አውጪዎችና የፓርላማ አባላት ፖሊሲዎቻቸውን የማጣጣም ስራዎችን ከወዲሁ መስራት እንዳለባቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡ ከጊዜ ጊዜ ተጨባጭ እድገት እያስመዘገበ ከመጣው የሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት በሻገር እንደ ኢጋድ፣ ኮሜሳ ፣ የአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግሥታት ባሉ ክልላዊና ዓለም ዓቀፍ ተቋማትም ሁለቱ ሀገራት በትብብር እየሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ሁለቱ ሀገራት ሰላም የራቃቸውን ሀገራት ሰላም ለማረጋገጥም በኢጋድ ማዕቀፍ ስር ተቀራርበው ስኬታማ ስራዎችን መስራታቸውን ዶክተር አቢይ አንስተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር  አቢይ የጅቡቲን  የወደብ አገልግሎትና ቴሌኮም ጨምሮ ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ይጎበኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም