የሰሜን ሸዋ ዞን ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሰማርተው የተለያዩ የልማት ስራዎችን በማከናወን ላይ ናቸው

72
ፍቼ ሀምሌ 27/2010 በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በበጎ ፍቃድ አገልግሎት የተሰማሩ ወጣቶች የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ በተለያዩ የልማት ስራዎች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን አስታወቁ። በዞኑ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከተሰማሩት ወጣቶች መካከል የኩዩ  ወረዳ በቄሬንሳ ቀበሌ በግብርና ሙያ አካባቢውን እያገዝ  የሚገኘው የሚዛን ቴፒ  ዩኒቨርስቲ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ወጣት ጥላሁን ካባ አንዱ ነው፡፡ ወጣቱ  እንደሚለው የእረፍት ጊዜውን በትውልድ መንደሩ በሚካሄድ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፍ የማጠናከሪያ ትምህርትና የግብርና ሥራዎች በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ይህም በአካባቢው ልማት ላይ የራሱን ተግባር በማከናወን ''በወጣትነቴ ምን ሰራሁ'' ከሚለው ወቀሳ ለመዳን እንደሚያስችለው ተናግሯል፡፡ የኮሌጅ አንደኛ ዓመት ተማሪ አብዱል ባሴጥ  ሃሰን  በአካባቢው የሚስተዋለውን የተፈጥሮ ሀብት መመናመንና የጽዳት ጉድለት በሚያሻሽሉ ስራዎች ላይ መሰማራቱን ገልጿል፡፡ በተጨማሪም አርሶ አደሩ ዘመናዊ አሰራርን እንዲለማመድ  የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ተናግሯል። “የተቸገረ መርዳት ከፍተኛ እርካታ ይሰጠኛል” ያለችው ደግሞ በግራር ጃርሶ  ወረዳ በኮትቾ ቀበሌ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሰማራችው ወጣት ፒሊሴ  ሞቱማ ናት፡፡ ሌሎች ወጣቶችም የእረፍት ጊዜያቸውን አልባሌ ስፍራ ከማሳለፍ ችግር ውስጥ ያለውን ወገናቸውን ባላቸው እውቀትና ጉልበት ሊረዱ እንደሚገባ ጠቁማለች። በፍቼ ከተማ እያገለገለ ያለው  የ3ኛ ዓመት የህግ  ተማሪ  ወጣት ስለሺ  በበኩሉ  የተደራጁ ክበባትን በእውቀትና ክህሎት ከማጠናከር ባለፈ ወጣቶች  የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ  ረገድ የራሳቸውን ሚና እንዲጫወቱ  የበኩሉን እያበረከተ መሆኑን ገልጿል፡፡ ወጣትነት ትኩስ ጉልበት ፣ በርካታ ፍላጐትና ስሜት የሚንፀባረቅበት የእድሜ ክልል መሆኑን የገለጸው ደግሞ ሌላው የከተማዋ ወጣት  ደርቤ ለቺሳ ነው። ወጣቶች የለውጥ ሃይል  እንዲሆኑ  ለሰላምና ፀጥታ ቅድሚያ  በመስጠት የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች ያለሁከት  በሰከነ ሁኔታ እንዲፈቱ የሚያስችል ትምህርት በመስጠት ላይ መሆኑን ገልጿል። የፍቼ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጅ  ተወካይ አቶ ገላን ዱኪ  ወጣቶቹ  በጽህፈት ቤታቸው ለበርካታ ጊዜ ተከማችቶ የቆየ  ፋይል በአጭር ጊዜ  በማደራጀት ለተገልጋዮች ምቹ ማድረጋቸውን አመልክተዋል፡፡ በወጣቶች ውስጥ የሚታየውን የሥራ መነቃቃትና ቅልጥፍናም አድንቀዋል። የሰሜን ሸዋ ዞን ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ  ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ታዬ በበኩላቸው በዞኑ ከ50  ሺህ  የሚበልጡ ወጣቶች በዘንድሮው የበጐ ፍቃድ አገልግሎት ተሰማርተዋል። በሁለት ወር ቆይታቸውም 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመት የልማት ስራ ያከናውናሉ ተብሎ ይበጠቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም