በመንግስት ተቋማት የሚስተዋለው ፍትሃዊነት የጎደለው አሰራርና አገልግሎት አሰጣጥ ሊስተካከል ይገባል....የሚዳ ወረሞ ወረዳ ነዋሪዎች

152
ደብረ ብርሃን ሐምሌ 27/2010 በሰሜን ሸዋ ዞን ሚዳ ወረሞ ወረዳ በመንግስት ተቋማት የሚስተዋለው ፍታሃዊነት የጎደለው አሰራርና አገልግሎት አሰጣጥ “ሊስተካከልልን” ይገባል ሲሉ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገለጹ። ነዋሪዎቹ በወረዳው የመንግስት ተቋማት በሚስተዋሉ የአሰራርና የመልካም አስታዳር ችግሮች ላይ ከአመራር አካላት ጋር ውይይት አካሂደዋል። በወረዳው የመራኛ ከተማ ነዋሪ ወጣት አባይነህ ወንድወሰን እንዳለው የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት ጥራት መጓደል በእለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ላይ ችግር እየፈጠረ ነው። በአካባቢው በመንገድ፣ በትምህርት፣ በጤናና በኮብል ስቶን ንጣፍ ስራዎችና በንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ግንባታ ላይ የጥራት ችግር ከመስተዋሉ በተጨማሪ ለረጅም ጊዜ በመጓተት የመንግስትና የህዝብ ንብረት እየተመዘበረ መሆኑን ተናግሯል። "ከአምስት ዓመት በፊት ለወረዳው ህዝብ የመብራት ማሰራጫ ዲስትሪክት ይገነባል ተብሎ ቃል ቢገባም እስካሁን ባለመገንባቱ የወረዳው ህዝብ ተገቢውን የኃይል አቅርቦት እያገኘ አይደለም" ሲሉም ቅሬታቸውን ገልጸዋል። በተጨማሪም "በወረዳው የወጣቶች መዝናኛ ማዕከላት፣ ቤተ መጻህፍት፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችና የኢፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማዕከል አለመኖራቸው ወጣቱ ጊዜውን በአልባሌ ቦታ እንዲያሳልፍ አስገድዶታል" ብሏል። ሆን ብለውና በዘመድ አዝማድ ለመጠቃቀም ሲሰሩ የቆዩ አመራሮችም ተለይተው በህግ  ሊጠየቁ እንደሚገባ ጠይቋል። አቶ ዳንኤል ማሞ የተባሉ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ በበኩላቸው በመንግስት ተቋማት ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ በጥቅማጥቅም ሰው እየተለየ የሚሰጥበት በመሆኑ መቸገራቸውን ገልጸዋል። በፍትህ አካባቢ በሃሰተኛና በተደራጁ ምስክሮች ንጹሃን ወገኖች ለእስር እየተዳረጉ በመሆናቸው በሚመለከተው አካል በኩል ተገቢውን የማጣራት ሥራ እንዲሰራ ጠይቀዋል። ወይዘሮ ሐና ሰለሞን የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው "በመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚካሄደው የሠራተኛ ምደባ፣ ቅጥርና ዝውውር ሙያን ታሳቢ ያደረገ ሳይሆን በዘመድ አዝማድ በመሆኑ ብቃት ያለው ሙያተኛ እየተመደበ አይደለም " ብለዋል። የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ መርከብ ለማ በበኩላቸው በህዝቡ የተነሱ ጥያቄዎችን በማጣራት ደረጃ በደረጃ ተገቢ ምላሽ እንደሚሰጥና ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል። ነዋሪዎች የጀመሩትን ሀሳባቸውን በዴሞክራሲያዊ መንገድ የመግለጽ ባህል በማሳደግ ለፀረ ሙስና ትግሉ፣ ለአገራዊ አንድነትና ለውጥ ተግተው እንዲሰሩ አሳስበዋል። የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር የህዝብ ቅሬታ ሰሚ መምሪያ ኃላፊ አቶ ጥላየ በላይ በበኩላቸው መንግስት ህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ ሲሰራ መቆየቱን ገልፀዋል። በመንግስት በኩል ጥረቱ ቢኖርም ከህዝቡ ፍላጎትና እድገት ጋር በተያያዘ በቂ አለመሆኑን ጠቁመው፣ በተለይ ከጥራትና ከተደራሽነት አንጻር የሚስተዋሉ ችግሮችን በቁርጠኝነት ለመፍታት አመራሩን የማጠናከር ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ፍትሃዊነት የጎደለው የሃብት አጠቃቀም እንዲስተካከል በነዋሪዎች የተነሳውን ቅሬታና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በጥልቅ ተሃድሶ በመለየት የማስተካከል ሥራ በማከናወን ላይ መሆኑንም አብራርተዋል። ከአመራሩ ጋር ተያይዞ አለ የተባለውን የአሰራርና በዘመድ አዝማድ የመስራት ችግር በጥልቀት በመለየት የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል። በአሁኑ ወቅት በ22 የወረዳው ቀበሌዎችና በሲቪል ሰርቪስ መስሪያቤቶች ህዝብ ተኮር ግምገማ መካሄዱን የገለጹት አቶ ጥላዬ፣ በቀሪ አምስት ቀበሌዎች ተመሳሳይ ግምገማ ከተካሄደ በኋላ በአጥፊዎች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል። በቀጣይም ችግሮች እስኪፈቱ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎች እንደሚቀጠሉ ጠቁመው፣ ህዝቡም በአሁኑ ውቅት የተጀመረው ለውጥ እንዳይደናቀፍ በተደራጀ አግባብ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል። በመረኛ ከተማ በተካሄደው ውይይትም የከተማው ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት ተቋማት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም