የሁዋዌ - አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአይ.ሲ.ቲ ልምምድ ማዕከል ተመረቀ

69

ግንቦት 24/2013 (ኢዜአ) የሁዋዌ-አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ (አይ.ሲ.ቲ) ልምምድ ማዕከል ተመረቀ።

የማዕከሉ መከፈት በኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚደረገውን እንቅስቃሴ እንደሚያግዝም ተገልጿል። 

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሙሉ ነጋ በምረቃው ላይ እንዳሉት፤ የማዕከሉ መከፈት ኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍን ለማሳደግ እየገነባች ላለው የዲጂታል ኢኮኖሚ አጋዥ ነው።

የዲጂታል ሽግግር ለማድረግና ቴክኖሎጂን ለማሳለጥ ለሚያግዘው ማዕከል የሚያስፈልጉ ግብአቶች በሁዋዌ በኩል እንዲሟላ መደረጉ ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና "ማዕከሉ ተወዳዳሪ የሰው ኃይል በማቅረብ መንግስት የቴሌኮም ዘርፉን ለማሳደግ የጀመረውን ሥራ ያግዛል" ብለዋል።

የማዕከሉ መከፈት በአይ.ሲ.ቲ ትምህርት ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎች እንዲሰለጥኑ፣ በዘርፉ የሥራ ዕድል እንዲያገኙና ለሀገራዊ ዕድገት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

ማዕከሉ ለጊዜው በዓመት 200 ተማሪዎችን የሚቀበል መሆኑን ገልጸው፤ "የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በትህምርት፣ በዕውቀትና በክህሎት ብቁ ሆነው እንዲወጡ የሚያደርገውን ጥረት የበለጠ ያጠናክራል" ብለዋል።

ዩኒቨርሲተው ያደረገው የፖሊሲ ማሻሻያና እራሱን ለማስተዋወቅ ያደረገው ጥረት ሁዋዌ በተቋሙ ማዕከሉን ለመክፈት አስተዋጽኦ እንዳደረገም ጠቁመዋል።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከአፍሪካ ምርጥ 10 ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ መሆኑ ከትላልቅ ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመስራት እንዳገዘውም ፕሮፌሰር ጣሰው ተናግረዋል።

የሁዋዌ ኩባንያ የሰሜናዊ አፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ሚስተር ፊሊፕ ዋንግ በበኩላቸው የማዕከሉ መቋቋም በዘርፉ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

ተማሪዎች በሚቀስሙት ልምድ የራሳቸውን አቅም ለማጎልበትና ሌሎችንም ብቁ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም