የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የባለሙያዎችን ስነ-ምግባር ችግር ለማስተካከል በትኩረት ሊሰራ ይገባል - የክልሉ ምክር ቤት አባላት

67
አሶሳ  ሀምሌ 27/2010 የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የውሳኔ አሰጣጥ ጥራት ለማሳደግና የባለሙያዎችን የስነምግባር ችግር ለማስተካከል በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የክልሉ ምክር ቤት አባላት ገለፁ፡፡ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ2010 በጀት ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት ትናንት በክልሉ ምክር ቤቱ ተገምግሟል፡፡ በዚሁ ወቅት የምክር ቤቱ አባል አቶ ደስታየሁ ምት እንደገለፁት በክልሉ የሚገኙ ፍርድ ቤቶች በወቅቱ ውሳኔ የመስጠት አቅም እያደገ ቢሆንም አሁንም የሚጓተቱ መዝገቦች አሉ፡፡ እንዲሁም በፍርድ ቤቶች ውሳኔ የሚሰጥባቸው መዝገቦችን ጥራት ለማሳደግ የፍትህ አካላት ማሰልጠኛ ማዕከል ሊቋቋም እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ከህዝብ ጋር በሚደረጉ ውይይቶች የስነ ምግባር ችግር ያለባቸው ዳኞች መኖራቸው በስፋት እንደሚነሳ የገለፁት አቶ ደስታየሁ በውሳኔ አሰጣጥ ላይ የሚታየው የጥራት ችግር ከዚህም የመነጨ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ወይዘሮ መሪየም የሱፍ የተባሉ ሌላዋ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው በክልሉ የህፃናት ልዩ ችሎት በተቋቋመባቸው ፍርድ ቤቶች በቂ ባለሙያ ሊመደብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ በክልሉ ያለው የተዘዋዋሪ ችሎት አፈፃፀም የተሻለ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቅጥል እንደሚገባ የገለፁት ደግሞ አቶ በላይ ወዲሻ ናቸው፡፡ የወረዳ ፍርድ ቤቶች ርቀት ባላቸው ቀበሌዎች ተዘዋዋሪ ችሎት የማስቻል አቅማቸው እንዲያድግ ድጋፍ ማድረግና የቅንጅት ስራ ሊጠናከር  እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ነጂ ኖኖ በ2010 በጀት ዓመት ለ20 ሺህ 700 መዝገቦች ውሳኔ በመስጠት ከ95 በመቶ በላይ አፈፃፀም ማስመዝገቡን ገልፀዋል፡፡ ውሳኔ ያገኙ መዝገቦች ጥራት የሚታወቀው በፍርድ ቤት ውሳኔ ተሰጥቶባቸው በይግባኝ የሚታዩ መዝገቦች ሲፀኑ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ከዚህ አንፃር የክልሉ ፍርድ ቤቶች የውሳኔ ጥራት 77 በመቶ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የውሳኔ ጥራቱን ለመጠበቅ የዳኞችን አቅም ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ገልፀው ለዚህም የፍትህ አካላት የስልጠና ማዕከል ለማቋቋም ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ የስነምግባር ችግር ያለባቸው ዳኞች ላይ እርምጃ መወሰዱንና በቀጣይም ይኸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡ የክልሉ ምክር ቤት በሰባተኛ መደበኛ ጉባዔ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአመቱን አፈፃፀም ሪፖርት ከነማሻሻያው በሙሉ  ድምጽ አጽድቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም