የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከ57 በላይ ማህበረሰብ ተኮር የምርምር ፕሮጄክቶች በማካሄድ ላይ መሆኑን ገለፀ

48
ጎባ ግንቦት 7/2010 የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከ57 በላይ ማህበረሰብ ተኮር የምርምር ፕሮጄክቶች በማካሄድ ላይ መሆኑን አስታወቀ፡፡ የዩኒቨርሲቲው የምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ስሜነህ ቤሴ ለኢዜአ እንደገለጹት በዩኒቨርሲቲው መምህራን በመካሄድ ላይ የሚገኙት ምርምሮች የማህበረሰቡን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ናቸው፡፡ ምርምሮቹ  በግብርና፣ ጤና፣ የተፈጥሮ ሀብት፣ የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ በሌሎች  መስኮች ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡ ለምርምርና የፕሮጄክት ስራዎቹ ዩኒቨርሲቲው ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የመደበበ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ፕሬዚዳንቱ በስራውም ከ100 የሚበልጡ መምህራንና የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ዓመታት በምሁራን ከተከናወኑት ምርምሮች መካከል የተመረጡትን በራሱና ዓለም አቀፍ እውቅና ባላቸው ጆርናሎች ላይ በማሳተም ለተጠቃሚው እንዲደረሱ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን አስረድተዋል ። በተጨማሪም በዩኒቨርሲቲው ምሁራን የሚቀርቡ ምክረ ሀሳቦችን እንደመነሻ  በመጠቀም በአካባቢው ከሚገኙ የመንግስት መስሪያ ቤቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ፕሮጄክት እየተቀረፀና ስልጠናና ድጋፍ እየተደረገ የማህበረሰቡን ችግር ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዶክተር ስሜነህ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው የአርሶና አርብቶ አደር ማህበረሰብ ችግር በቅርበት ተደራሽ ለማድረግና የቴክኖሎጂ ሽግግሩንም ለማቀላጠፍ  የምርምር ጣቢያዎችን በሮቤ፣ መዳ ወላቡና ጊኒር ወረዳዎች ከፍቶ እየሰራ ነው ። ከመዳ ወላቡ ወረዳ አርብቶ አደሮች መካከል አቶ ኢሰማኤል አብዱልቃድር እንደተናገሩት “ ዩኒቨርሲቲው በአካባቢያቸው የከፈተው የምርምር ጣቢያ ከተሻሻሉ የእንስሳት መኖ ዝሪያና የአመራረት ዘዴ ጋር አስተዋውቆኛል”  ብለዋል፡፡ ሌላው የወረዳው አርብቶ አደር መሐመድ ከማል በበኩላቸው “ የምርምር ጣቢያው በመስመር የመዝራት ቴክኖሎጂን ጨምሮ ከሌሎች የተሻሻሉ የግብርና ኤክስቴንሽን ዘዴዎች ጋር እንድተዋወቅና ቴክኖሎጂውን እንድጠቀም ረድቶኛል”  ሲሉ ገልፀዋል ፡፡ የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ከ390 በላይ ምርምሮችና የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክቶችን ማከናወኑን ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያመለከታል ፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም