ኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ጠንካራ የባለድርሻ አካላት የጋራ ድጋፍ ያስፈልጋታል ተባለ

99
አዲስ አበባ ሀምሌ 27/2010 ኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን በተሻለ መልኩ ለማረጋገጥ  የባለድርሻ አካላት ጠንካራ ድጋፍ የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ መሆኗን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። የአፍሪካ ሴቶች የትምህርት ባለሙያዎች ፎረም (ፋዌ) ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ከሚባለው ግብረሰናይ ድርጅት ጋር በመሆን ድጋፍ ሲያደርግላቸው የቆዩ 12ኛ ክፍል ያጠናቀቁ ተማሪዎችን አስመርቋል። የአፍሪካ ሴቶች የትምህርት ባሙያዎች ፎረም (ፋዌ) በኢትዮጵያ ለሁለት አስርት ዓመታት ገደማ በወንዶችና በሴቶች መከካል የሚታየውን የትምህርት ተደራሽነት ልዩነት ለማጥበብ ሲሰራ የቆየ ድርጅት ነው። ግብረ ሰናይ ድርጅቱ ከፍተኛ የትምህርት ፍላጎትና ችሎታ ኖሯቸው ግን ደግሞ አቅም ለሌላቸው 75 በመቶ ሴቶችና 25 በመቶ ወንዶችን ሲረዳ መቆየቱም ተገልጿል። የድርጀቱ የኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ደገፋ እንደሚሉት ዛሬ የተመረቁት 12ኛ ክፍል ያጠናቀቁ ተማሪዎች በድርጅቱ ድጋፍ እየተደረገላቸው ከሚገኙ 800 ተማሪዎች መከካል 100ዎቹ ናቸው። በእዚህ እድል የተካተቱ ተማሪዎች ድርጅቱ የ10 ዓመት መርሃ ግብር ነድፎ ከሚሰራባቸው ከአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ክልልና በአዲስ ከተማ አስተዳደር ስር ከሚገኙ የተመረጡ ትምህርት ቤቶች የተወጣጡ ናቸው ብለዋል። ድርጅቱም በትምህርታቸው የተሻሉ ተማሪዎችን መልምሎ የተለያዩ የክህሎት ስልጠናዎች የመስጠት፣ የትምህርት ግብዓት የማቅረብ፣ የኪስ ገንዘብና ለተማሪዎቹ የሚያስፈልጉትን ነገሮች እያሟላ ቆይቷል ነው ያሉት። በቀጣይ እነዚህ ተማሪዎቹ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚቀላቀሉ በመሆኑ የድርጅቱ ድጋፍ ለሌሎች የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ጋር ይቀጥላል ብለዋል። የዕድሉ ተጠቃሚ ከሆኑ ተማሪዎች መካከል ተማሪ ሶስና ተስፋዬና ተማሪ አሸናፊ ዋለ ያገኙት ድጋፍ የበለጠ በትምህርት ላይ እንዲያተኩሩ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ። የቦሌ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ የነበረችው ሶስና ተስፋዬ ''እናቴ እኔን ጨምሮ ሶስት ቤተሰቦችን ታስተዳድራለች፣ ያገኘሁት ድጋፍ የእናቴን ጫና ቀንሶላታል'' ብላለች። ''ድጋፉ ክህሎትና እውቀቴ፣ በራስ መተማመኔ እንዲጎለብት ዕድል ፈጥሮልኛል'' ያለቸው ተማሪዋ በቀጣይም በተለያዩ የሕብረተሰብ አገልግሎት ውስጥ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኗን ተናግራለች። ሌላው ከባህርዳር የድጋፉ ተጠቃሚ የሆነው ተማሪ አሸናፊ ዋለ ''ያገኘሁት ዕድል ሙሉ ትኩረቴ ትምህርት ላይ እንዲሆን ስላስቻለኝ ውጤታማ ሆኛለሁ'' ብሏል። ወደ ፊትም ለአገር የጎላ ፋይዳ ሊኖራቸው የሚችሉ የጥናትና የምርምር ስራዎችን ለማከናወን ዕቅድ እንዳለው ተናግሯል። በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትር ደኤታው አቶ ተሾመ ወዳጆ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በትምህርት ተደራሽነት ረገድ እጅግ ስከኬታማ ተግባራት አከናውናለች ብለዋል። በተለይ ደግሞ የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ በማሳደግ ረገድ በመጀመሪያ ደረጃ 105 በመቶ፣ በሁለተኛ ደረጃ 45 ነጥብ 2 በመቶና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት 35 በመቶ ማድረስ ተችሏል ነው ያሉት። በቀጣይም አገሪቷ የትምህርት ጥራትን ለማምጣት በትኩረት እየሰራች ትገኛለች ያሉት ሚኒስትር ደኤታው ይህን ለማሳካት ደግሞ የባለድርሻ አካላት የጋራ ድጋፍና ርብርብ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። በተለይ ደግሞ የአፍሪካ ሴቶች የትምህርት ባለሙያዎች ፎረም (ፋዌ)ን የመሳሰሉ ድርጅቶች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል። ፋዌ በ34 የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ለሚገኙ ጥሩ አዕምሮ ኖሯቸው ትምህርት ለማግኘት የአቅም ችግር ያለባቸውን ተማሪዎች የሚረዳ ሲሆን በተለይ ደግሞ ትልቁን ትኩረት ለሴት ተማሪዎች ይሰጣል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም