በሀገር ህልውና ላይ አደጋ ለመፍጠር በሚጥሩ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ላይ እርምጃ ለመውስድ እንገደዳለን - ባለስልጣኑ

70

አዲስ አበባ ግንቦት 23 ቀን 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን፤ ኃላፊነት በጎደለው መልኩ በሀገር ህልውና ላይ አደጋ ለመፍጠር በሚጥሩ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ።

እስካሁን ባለው ሂደት 30 የሚጠጉ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን በፈቃደኝነት ተመዝግበው ወደ ህጋዊ አሰራር መግባታቸውንም ይፍ አድርጓል።

የዲጂታል ቴክኖሎጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ እያደገ መምጣቱ ጋር ተያይዞ በርካታ ሰዎች የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃንን ይከታተላሉ።

የዲጅታል ቴክኖሎጂ  እድገትና  ቴክኖሎጂውን በሚጠቀሙ ሰዎች  ያለው የእውቀት ውስንነት ደግሞ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃንን በቀላሉ ለሀሰተኛ መረጃና ሌሎች ዓላማዎች ማስፈጸሚያ እያደረጋቸው መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ይጠቁሟሉ።

በኢትዮጵያም ከ21 ሚሊዮን በላይ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ያለ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውሰጥ በርካቶች የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃንን ይከታተላሉ።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እንድሪስ፤ ለሀገር ህልውና እና ለዜጎች አብሮነት የሚሰሩ የበይነ መርብ መገናኛ ብዙሃን የመኖራቸውን ያህል ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ጥቅማቸውን ብቻ የሚያሳድዱ እንዳሉ ይናገራሉ።

ከተመልካች የሚያገኙትን ገንዘብ ከማሳደድ ባለፈ የሚያሰራጩት መረጃ በሀገር ህልውና እና ጥቅም ላይ ስለሚያስከትለው ጉዳት ግድ የማይሰጣቸው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን መኖራቸውንም ነው የተናገሩት።

እነዚህ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ከመረጃ ትክክለኝነት ይልቅ መረጃው ተሰራጭቶ የሚያስገኘው ገቢ የሚያስጨንቃቸው፤ መልእክት መጋራትን ከሀገር ጥቅም የሚያስበልጡ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ከዚህ አንጻር የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃንን ወደ ህጋዊ አሰራር የሚያስገባ ዘዴን ቀይሶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተናግረዋል።

ባለስልጣኑ በቅርቡ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን እንዲመዘገቡ ያስተላለፈውን ጥሪ ተከትሎ 30 የሚሆኑትን መመዝገብ መቻሉን አንስተዋል።

ለተመዘገቡት የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ደግሞ ህጋዊ ከለላን ከመስጠት ጀምሮ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረግላቸዋል ነው ያሉት።  

እስካሁን ያልተመዘገቡና መመዝገብ የሚፈልጉ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር ቀርበው መነጋገር እንደሚችሉም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

ሀገር ህልውና ላይ አደጋ ለመፍጠር በሚጥሩ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ላይ ወቅቱን የሚመጥን ቁጥጥር የሚደረግ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈ ኃላፊነት በጎደለው መልኩ የሀገር ህልውና ላይ አደጋ ለመፍጠር በሚጥሩት ላይ ግን ህጋዊ እርምጃ ለመውስድ እንገደዳለን ብለዋል።

መንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በህጋዊ መንገድ ለተመዘገቡ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን መረጃ ከመስጠት ጀምሮ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉላቸውም ጥሪ አቅርበዋል።

የበይነ መረብ ተጠቃሚ ዜጎችም ሀሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ የትስስር ገጾችን ባለመከተልና መልእክቶቻቸውን ባለማጋራት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 በበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ለመስራት የሚፈልጉ አካላት ከባለስልጣኑ የምዝገባ ምስክር ወረቀት ማውጣት እንዳለባቸው ይደነግጋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም