የዘመነ መሳፍንትን ታሪክ ዘካሪው መፅሐፍ

485

የታሪክ ሊቃውንት ያደነቁት የዘመነ መሳፍንትን ታሪክ ዘካሪው መፅሐፍ

በአየለ ያረጋል /ኢዜአ/


በዘመነ መሳፍንት ታሪክ ላይ ያተኮረውና የታሪክ ሊቃውንት ያደነቁት የደራሲና ጋዜጠኛ ገነት አየለ አንበሴ 'በኢትዮጵያ ተራሮች ቆይታዬ' የተሰኘው ቅፅ 2 የትርጉም መፅሐፍ ተመርቋል።


ትናንት ማምሻውን በስካይላይት ሆቴል በተካሄደው መፅሐፍ ምረቃ ስነ ስርዓት ታላላቅ ኢትዮጵያን የታሪክ ሊቃውንት፣ የቀድሞ ጦር መኮንኖች፣ የኪነ ጥበብ ሰዎችና የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የደራሲዋ 5ኛ መፅሐፍ የሆነው በኢትዮጵያ ተራሮች ቆይታዬ ክፍል ሁለት መፅሐፍ በ2009 ዓ.ም በደራሲዋ ከፈረንሳይኛ ወደ አማርኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ለንባብ የበቃው የአርኖ ሚሸል ዳባዲ 'በኢትዮጵያ ተራሮች ቆይታዬ ክፍል አንድ' ተከታይ ነው። 


ደራሲው አርኖ ሚሸል ዳባዳ ኢትዮጵያ በዘመነ መሳፍንት ጨለማ ውስጥ በነበረችበት ዘመን ከወንድሙ አንቷን ሚሸል ዳባዲ ጋር ከትውልድ ሀገሩ ፈረንሳዊ ለግል ጥናትና ምርምሩ ወደ ኢትዮጵያ ተጉዞ ከ1837 እስከ 1848 ለ12 ዓመታት የኖረ አሳሽ ነው። በኢትዮጵያ ቆይታውም ከትግራይ፣ ስሜን፣ ጎንደርና ጎጃም መሳፍንት ጋር በቅርበት ኖሮ የኖረበትን ማስታወሻ በ4 ተከታታይ ቅፆች ፅፎታል። 


በመድረኩ ሒሳዊ አስተያይት ያቀረቡ የታሪክና የቋንቋ ሊቃውንትም በገነት አየለ ተተርጉሞ የቀረበው የአርኖ ሚሸል ዳባዲ መፅሐፍን ያልተነገረ ታሪክ ያወሳ ድንቅ መፅሐፍ ስለመሆኑ መስክረዋል። 


የታሪክ ተመራማሪው አበባው አያሌው (ረዳት ፕሮፌሰር) አርኖ ሚሸል ዳባዲ ከሌሎች አውሮፓውያን የዘመነ መሳፍንት አሳሾች/ተጓዦች በተለዬ የዘመኑን የኢትዮጵያ ታሪክ የመዘገበ አጥኚ መሆኑን አንስተዋል። 


ለአብነትም ዳባዲ እንደሌሎች አውሮፓውያን አሳሾች የአገሩን መንግስት ተልዕኮ ይዞ ሳይሆን በግል ፍላጎቱ ኢትዮጵያን መጎብኘቱ፣ በርካታ መሳፍንትን በቅርበት ማወቁ፣ ከሰሜን ኢትዮጵያ እስከ እናርያ ተዘዋውሮ መመልከቱና ትዝብቱንም ቁልጭ አድርጎ መፃፉ ከሌሎች የተለዬ ያደርገዋል ነው ያሉት። 


ለአብነትም በዘመኑ ወደ ኢትዮጵያ የመጣውና የዘመነ መሳፍንትን ጉዳይ ከፃፉት መካከል የሚጠቀሰው እንግሊዛዊ ናትናኤል ፒርስ በትግራይ ብቻ በመቆየቱ የኢትዮጵያን ዘመነ መሳፍንት ሙሉ ስዕል የሚይዝ ዘገባ እንዳልፃፈ አንስተዋል። አርኖ ዳባዲ ግን ከትግራይ መሳፍንት ባሻገር የስሜኑን ደጃዝማች ውቤ፣ እቴጌ መነንና ልጇን ትንሹ ራስ አሊ እና የጎጃም ገዥዎች ደጃዝማች ጎሹ ዘውዴንና ደጃች ብሩ ጎሹን እልፍኝ ድረስ ዘልቆ የመሳፍንቱን ስብዕና፣ ፖለቲካዊ አሰላለፍና ስርዓቱን ጠንቅቆ ማወቅ አስችሎታል ብለዋል።

በሌላ በኩል እንደ ጀምስ ብሩስ መሰል አሳሾች ራሱን የኮፈሰና የኢትዮጵያን ባሕል ሳይረዳ ያንኳሰሰ ሳይሆን የማህበረሰቡን አኗኗር በተግባር የኖረ ብሎም ባህሉን፣ ቋንቋውንና ስርዓቱን ተረድቶ የፃፈ አንትሮፖሎጂስትና የታሪክ ተመራማሪ ተጓዥ እንደሆነም አንስተዋል።


ከመፅሐፍ ይዘት ከጠቀሷቸው ነጥቦች መካከልም የሴቶችን የፖለቲካ ሚና፣ ከአፄ ቴዎድሮስ በፊት አንዱ አንዱን ጥሎ ለመንገስ የነበረውን የመሳፍንት ሽኩቻና መሳፍንቱ በስርዓቱ አልበኝነት ቢሻኮቱም የዘውድና ሐይማኖታዊ ስርዓት እንደነበሩ መፅሐፉ በግልጽ ያሳያል ነው ያሉት። በጥቅሉ "የዘመነ መሳፍንት ታሪክ ነጋሪ" በሚል የገለፁት የዳባዲ መፅሐፍ ተተርጉሞ መቅረቡ ለታሪክ ተመራማሪዎች አጥኝዎች እና አንባቢዎች ትልቅ ስጦታ ነው ብለዋል። 


ከመፅሃፉ የአማርኛ ትርጉም ሕትመት ቅርፅ ጋር በተያያዘ በቀጣይ ሕትመት የአንዳንድ የቦታ ስሞች ማረሚያ እንዲደረግ፣ አባሪዎችና የጥንታዊ ቦታዎችን መገኛ የሚጠቁም ካርታ ቢቀመጥለት የሚል ጥቆማ ሰጥተዋል። 


ሌላው የቋንቋና የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ፤ ፀሐፊው አርኖ ዳባዲ የእያንዳንዱን መሳፍንት ግለ ስብዕና ጨምሮ የዘመኑን የፖለቲካ አሰላለፍና የፊውዳሊዝም ስርዓት በሚገባ የሚያስረዳ መሆኑን ገልፀዋል። 


መፅሐፉ የዘመነ መሳፍንት የታሪክ መስታወት ነው ያሉት ፕሮፌሰር ፍቅሬ፤ በአማርኛ ተተርጉሞ መታተሙ ለተመራማሪዎች ትልቅ ግብዓትነት የሚውል ጠቃሚ ስራ መሆኑን አንስተዋል። በጋዜጠኛ ገነት አየለ የቀረበው የአማርኛው ትርጉምም፣ የትርጉም ሳይሆን ወጥ ስራ እስኪመስል ድረስ በተባ ቃላትና ትረካ የቀረበ ግሩም ስራ ነው ሲሉ አድንቀዋውታል።

አንጋፋው ደራሲና ጋዜጠኛ አበራ ለማ በበኩሉ አርኖ ሚሸል ዳባዲ የጨለማ ዘመን በሚሰኘው ዘመነ መሳፍንት የሰማውን ሳይሆን በድርጊቱ ሁሉ የተሳተፈ ከሌሎች አሳሾች የሚለይ የውጭ ዜጋ እንደሆነ ገልፇል። 


የግድያ፣ የሽኩቻ፣ የጦርነት ዘመን በነበረው ዘመነ መሳፍንት የገዢዎች ጭካኔና ነውር እንዲሁም ወንበር ለመያዝ ሴቶች የሚደርስባቸው መጥፎ ዕጣ ፈንታ በመፅሐፉ በጉልህ እንደተቀመጠ ገልፀዋል። 

ዳሩ ይህ የዘመነ መሳፍንት የጭካኔና የግፍ ተግባር ግን በዘመነ መሳፍንት ብቻ ሳይሆን በዘመነ ነገስታትም ሆነ እስካሁን ባሉ የኢትዮጵያ ስርዓተ መንግስታት እንዳልተላቀቀ አንስተዋል። ታሪክ ዘጋቢው በመሳፍንቱ ዘንድ በተለይም በደጃዝማች ጎሹ ውስጥ በወታደራዊና አስተዳደራዊ አገልግሎት የዋለ፣ በአማካሪነት የሰራ፣ ከፈረንሳዊነት ይልቅ ሀበሻነት ጎልቶ የሚሰማው የሚመስል ሰው እንደሆነ አብራርቷል። 


የአፃፃፍ ብቃቱም ከመናገር ይልቅ ስዕላዊ አተራርክ ያለውና ረቂቁን አጉልቶ የሚያሳይ ብዕር እንዳለው ጠቅሷል። 


ዳቫዲን የመሰለ የታሪክ ፀሐፊ የጨለመውን ዘመነ መሳፍንት በታሪክ መዘክርነት ቀጣይ ትውልድ እንዲያውቅ አድርጓል፤ የገነት አየለ የትርጉም ስራዎችም ከትርጉም ይልቅ ወጥ ስራዎች ይመስላሉ በማለት የፕሮፌሰር ፍቅሬን ገለፃ ተጋርቷል።


"የገነት አየለ ትርጉም መፅሐፍት ፈጠራ ይመስላሉ" ያለው ደግሞ አንጋፋው ባለቅኔና ፀሐፈ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ ነው። 


ትርጉም የማናውቀውን ለመረዳት ሚናው የጎላ በመሆኑ ተርጓሚዋን አድንቀው፣ በኢትዮጵያዊያን የተፃፉ የስነ ፅሁፍ ስራዎችም ተነባቢ በሚያደርጉ የውጭ ቋንቋዎች ተተርጉመው ቢቀርቡ ሲል ጠይቋል። 


ሌላው በመድረኩ የተናገሩት የኢሕድሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ፋሲካ ሲደልልም ለታሪክ ግብዓት የሚውል ትልቅ ስራ በመቅረቡ ተርጓሚዋን አመስግነዋል። የፈረንሳይኛ ቋንቋ የሚችሉ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ቢኖሩም እንዲህ አይነት ውብ ስራዎችን ተርጉሞ ማቅረብ እንዳልቻሉ አንስተዋል። 


እንደ ምጣኔ ሀብት ምሁርና እድሜ ባለፀጋ የዘመነ መሳፍንት በግብርናው ዕድገት ያሳደረው ተፅዕኖ እንዲሁም ከዘመነ መሳፍንት የእርስ በርስ ጭፍጨፋ ምን ተማርን የሚለው እንደሚያሳስባቸው አንተስተዋል። 


ከ40 ዓመታት በፊት በነበረው አዕምሮዩ ቢሆን ይህን አላስብም ነበር ያሉት አቶ ፋሲካ ሲደልል፣ ዛሬ ግን በኃይለስላሴ የታህሳሱ ግርግር፣ እርሳቸው በነበሩበት የደርግ ዘመንም ከ60ዎቹ መኳንንት ግድያ እስከ ነጭና ቀይ ሽብር፣ በወያኔ ዘመንም ሆነ ዛሬም ድረስ የእርስ በርስ ግድያዎችና ጭካኔዎች ከዘመነ መሳፍንት የተወረሰ ግብር መሆኑን ገልፀው፣ በዚህ ጉዳይ ልንነጋገርበት ይገባል የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።

በሐረር ቀላድ አምባ ተወልዳ ያደገቺው ደራሲና ጋዜጠኛ ገነት አየለ በኢትዮጵያ በቴሌቪዥን ድርጅት በጋዜጠኝነት ሰርታለች።


ከደርግ መንግስት ውድቀት በኋላም ወደ ነፃው ፕሬስ ገብታ በተለያዩ መፅሔቶች በአዘጋጅነትና በአሳታሚነት ተሰማርታ ለእስር እስክትዳረግ ድረስ በጋዜጠኝነት ሙያ አገልግላለች። ቀጥሎም ኑሮዋን በአገረ ፈረንሳይ አድርጋለች። የቀድሞውን የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም በስደት ከሚገኙበት ዝምባብዌ (ሐረሬ) በመሄድ የመንግሥቱ ኃይለማርያም ትዝታች (ቅፅ 1 እና 2) በሚል ፅፋለች። በሩዋንዳ ጎሳዎች (ሁቱና ቱቱሲ) ዘር ተኮር ጭፍጨፋን በሚመለከት በፈረንሳይኛ ቋንቋ የተፃፈን መፅሐፍም 'ትንሿ ሀገር' በሚል ወደ አማርኛ ተርጉማ ለንባብ አብቅታለች። የዳባዲ ሁለት ቅፆች ጋርም በድምሩ ስራዎቿን አምስት አድርገውታል። ቀጣይ የዳባዲ ክፍል 3 እና 4 መፃሕፍትን ተርጉማ እንደምታቀርብ ቃል ገብታለች።


ደራሲው ዳቫዲ በመፅሐፉ መቅድም ባስቀመጠው (ሰኔ-1868) የምሁራኑን አስተያየትና የመፅሐፉን ይዘት በሚደግፍ አግባብነት እንዲህ አስቀምጦታል።

"በ1836 ዓ.ም ወደ ምስራቃዊ ከተጓዝኩ በኋላ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ተራሮች ላይ ከሕዝቡ ጋር ኖሬ ለመጨረሻ ጊዜ ወደ አገሬ ተመልሸ የመጣሁት በ1862 ዓ.ም ነበር። እዚያ በከረምኩበት የአስራ ሁለት ዓመት ቆይታዬ እንደተመልካች ሆኜ መታዘብ ብቻ ሳይሆን እንደ አገር ተወላጅ የዕለት ተዕለት ኑራቸውን ኖሬያለሁ። በመፅሐፌ ውስጥ የገለፅኳቸው የጦርነትም ሆነ ሌሎች አጋጣሚዎች ላይ በቀጥታ ተካፍያለሁ። ዛሬ የድፍን አውሮፓ ትኩረት ወደዚያች አገር እንዲሳብ ያደረጉ ሁኔታዎች ሲፈፀሙ እዚያው ነበርኩ። ...በእኔ አስተያየት በሌሎች ህዝቦች መካከል ለረጂም ጊዜ ስንቆይ የተወለድንበትን አገር ሕዝብ አመለካከትና አተያይ እንደገና ልንለምደውና ልንገነዘበው ይገባል። ይህም አስፈላጊ ከሆነ ግምት፣ የተዛባ አመለካከትና ያልሆነ አስተያየት እንድንቆጠብ ያግዘናል" በማለት ፅፏል።


በ8 ምዕራፍ የቀረበው በኢትዮጵያ ተራሮች ቆይታዬ ክፍል ሁለት መፅሐፍ በ247 ገፆች ተቀንብቦ በ200 ብር ለገበያ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም