በአዲስ አበባ የደረጃ ”ሐ” ግብር ከፋዮች የግብር ማሳወቂያ ጊዜ እንደማይራዘም ተገለጸ

176
አዲስ አበባ  ሀምሌ 27/2010 በአዲስ አበባ የደረጃ ”ሐ” ግብር ከፋዮች የግብር ማሳወቂያ ጊዜን እንደማያራዝም የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለስልጣን አስታወቀ። የደረጃ ”ሐ” ግብር ከፋዮች የግብር ማሳወቂያ ጊዜ የፊታችን ሰኞ ሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓም የሚጠናቀቅ ቢሆንም ግብር ከፋይ ነጋዴዎች በግብር ማሳወቂያ መርሃ-ግብር መሰረት ግብራቸውን እየከፈሉ አለመሆኑን ባለስልጣኑ አስታውቋል። ከግብር ከፋይ ማህበረሰቡ ውስጥ በተሰጠው የጊዜ ገደብ መሰረት ግብሩን ያላሳወቀው እጅግ በርካታ መሆኑን የባለሰልጣኑ ኮሙኑኬሽን ቡድን አስተባባሪ አቶ አዳነ ገብረእግዚአብሔር ተናግረዋል። እርሳቸው እንዳሉት በመዲናዋ በደረጃ ”ሐ” አለ ተብሎ ከሚታሰበው 213 ሺህ  ግብር ከፋይ መካከል በተሰጠው የጊዜ ገደብ መሰረት እስካሁን ግብራቸውን ያሳወቁት ከ128 ሺህ አይበልጡም። ለዚህም ምክንያቱ "ከቀነ-ገደቡ ውጭ ተጨማሪ ጊዜ ይሰጣል" የሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ እንዳለ ገልፀዋል። በተሰጠው የጊዜ ገደብ ዓመታዊ ግብራቸውን ለማያሳወቁ ግብር ከፋዮች ተጨማሪ ጊዜ እንደማይጨመር ባለስልጣኑ አስታውቋል። የአዲሰ አበባ ግብር ከፋይ መደበኛውን ግብር የማሳወቂያ መርሃ -ግብር ጊዜ ገደቡ መሰረት ግብሩን እንዲያሳወቅ ባለስልጣኑ አሳስቧል። ባለስልጣኑ የግብር አሰባሰብ አቅሙን ለማሻሻል ቅዳሜ ሙሉ ቀንን ጨምሮ  አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ በቀሩት ሶስት ቀናት ግዴታውን አንዲወጣም አቶ አዳነ አሳስበዋል። በግብር አዋጁ መሰረት ግብራቸውን በጊዜው በማያሳወቁ ነጋዴዎች ላይ ባለስልጣኑ ወለድን ጨምሮ ሌሎች የቅጣት እርምጃዎችን በመውሰድ ጭምር ግብሩን ለማስከፈል እንደሚገደድም አስታወቀዋል። ባለስልጣኑ እስከ ጥቅምት 30 ከደረጃ ሐ፣ ለ፣ እና ሀ ከግብር ከፋዮች ለመሰብሰብ ካቀደው 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ውስጥ እስካሁነ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ሰብስቧል። በሀገሪቱ የግብር ህግ መሰረት የደረጃ ”ሐ ግብር ከፋዮች እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም፣ የደረጃ ”ለ” እስከ ጳግሜ አምስት 2010 ዓ.ም እንዲሁም የደረጃ ” ሀ” ግብር ከፋዮች እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ግብራቸውን ማሳወቅ አለባቸው። በተያዘው በጀት ዓመት በአዲስ አበባ ገቢዎች ባለስልጣን 34 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም