የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለተጓዦች የጉብኝት መርኃ ግብር ሊጀምር ነው

74
አዲስ አበባ ሀምሌ27/2010 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ቀጣይ በረራቸውን ለሚያደርጉ ዓለም አቀፍ ተጓዦች የጉብኝት መርኃ ግብር ሊጀምር ነው። የአገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ ለማስተዋወቅ ያለመው ይኸው አዲስ አሰራር በመጪው ነሃሴ 26 በይፋ ይጀመራል ተብሏል። አየር መንገዱ እንዳስታወቀው፤ ተጓዦቹ በኢትዮጵያ በርካታ ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ኃይማኖታዊና ተፈጥሯዊ መስህቦችን ያለ ተጨማሪ ክፍያ ለማየት ያስችላቸዋል። ለዓለም አቀፍ ተጓዞች ይህንን እድል ለመጠቀም የሚያስችላቸውን ቪዛ በተቋሙ በይነ መረብ ላይ መመዝገብ እንደሚኖርባቸው ተጠቅሷል። የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም እንደተናገሩት፤ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አገሪቱን የቱሪዝም መዳረሻ አማራጭ ለማድረግ እየተሰራ ነው። ''አገሪቱ ምንም እንኳን ቱባ የቱሪዝም ባለቤት ብትሆንም ዓለም አላወቃትም'' ያሉት ሥራ አስፈጻሚው ዘርፉ ለውጭ ምንዛሪ ግኝትና ለሥራ እድል ፈጠራ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል። በመሆኑም አሁን የሚጀመረው የጉብኝት መርኃ ግብር በኢትዮጵያ አልፈው የሚሄዱ ተጓዞችን ለመሰብሰብና ወደ አገሪቱ የሚፈሰውን የቱሪዝም እድል ከፍ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም