ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና ዶክተር ሬክ ማቻር የሰላም ስምምነት በካርቱም ሊፈራረሙ ነው

1640

አዲስ አበባ  ሃምሌ 27/2010 የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት እና ምክትላቸው በነበሩት ዶክተር ሪክ ማቻር መካከል የነበረውን የእርስ በርስ ግጭት የሚፈታ አዲስ የሰላም ስምምነት እሁድ ሐምሌ 29 ቀን 2010 ዓ.ም. በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ሊፈራረሙ ነው።

በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ፒ ሞርጋን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ በካርቱም የሚካሄደው የሰላም ስምምነት ፊርማ በአገሪቱ የነበረውን የእርስ በርስ ግጭት የሚያስቀር ነው።

የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ሊቀመንበር እና የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተገኙበት በሁለቱ ወገኖች መካከል የሰላም ስምምነት ፊርማው እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።

በደቡብ ሱዳን የተፈጠረውን የእርስ በርስ ግጭት የዜጎችን ስቃይና እንግልት እንዲያበቃ ኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና በቀድሞ ምክትላቸው ዶክተር ሪክ ማቻር መካከል የሰላም ድርድር ስታደርግ መቆየቷን ተናግረዋል።

እንደ አምባሳደር ሞርጋን ገለጻ፤ በደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች ሳቢያ በንጹሃን ዜጎች እንዲሁም በአጠቃላይ በአገሪቱ ያለው ስቃይ እና እንግልት ለማቆም የካርቱም የሰላም ስምምነት የመጨረሻ ይሆናል።

ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ዶክተር አብይ አህመድን ወደ አገራቸው ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት እንደሚጋብዟቸው አምባሳደር ሞርጋን ገልጸዋል።

እንደ አገር ከተመሰረተች አንድ አስርት ያልሆናት ደቡብ ሱዳን ነፃነቷን ከአወጀች ሁለት ዓመት በኋላ እ አ አ በ2013 የፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ምክትል የነበሩት ዶክተር ሪክ ማቻር መፈንቅለ መንግስት አሲረዋል በሚል ግጭት በመፈጠሩ የተነሳ ወደ እስስ በርስ ጦርነት ማምራቷ የሚታወስ ነው።

ግጭቱ እንደተከሰተ 2ነጥብ2 ሚሊዮን የሚሆኑ የአገሪቱ ዜጎች ከቀዬአቸው ለመፈናቀል ተገደዋል።

ከዚያን ጊዜ አንስቶ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከቀዬአቸው በመፈናቀላቸው ለስቃይና ለእንግልት ተዳርገዋል።

በፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና ዶክተር ሪክ ማቻር መካከል የተፈጠረውን ቀውስ ለመፍታትና አገሪቱን ወደ ሰላም ለመመለስ በኢጋድና በተለያዩ አለም ዓቀፍ ተቋማት በኩል በሚደረግ ጥረት ሁለቱ አካላት ተገናኝተዋል።