የገበያ እጦት ከምርታችን ተገቢውን ጥቅም እንዳናገኝ እያደረገ ነው - የአርሲና ምስራቅ ሸዋ ዞን አርሶ አደሮች

49
አዳማ ሀምሌ 27/2010 የገበያ እጦት ከምርታችን ተገቢውን ጥቅም እንዳናገኝ እያደረገ ነው ሲሉ በአርሲና ምስራቅ ሸዋ ዞን በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች  ገለጹ። አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት አርሶ አደሮች እንደተናገሩት የገበያ ችግር በደላሎች ተዕፅኖ ሥር በመውደቅ  ለኪሳራ እየዳረጋቸው ነው፡፡ በአርሲ ዞን ዲገሉ ጥጆ ወረዳ አሻ ሩክቻ ቀበሌ አርሶ አደር ፈይሳ ገመዳ በሰጡት አስተያየት ድንች፣ ጥቅል ጎመን፣ ቲማትም፣ ሽንኩርትና ሌሎች ምርቶችን በስፋት እያመረቱ ቢሆንም የገበያ ችግር ከምርቱ ተገቢውን ጥቅም እንዳያገኙ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ይህን የተረዱ ደላሎችም ማሳ ድረስ በመግባት ዋጋ እንደሚቆርጡባቸው ተናግረዋል፡፡ ''ደላሎች ዋጋ ቆርጠው ከሄዱ በኋላ ምርቱን ለመግዛት የሚጠይቅ አካል የለም'' ያሉት ደግሞ በምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ ቆቃ ኤጄርሳ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ተሾመ ከበደ ናቸው። ''አርሶ አደሩ ያለው አማራጭ ደላሎች ባሉት ዋጋ መሸጥ ብቻ ነው'' ያሉት አቶ ተሾመ በመንግስት መፍትሄ ሊበጅለት እንደሚገባ ጠይቀዋል። የመቂ ባቱ አትክልትና ፍራፍሬ አምራች ህብረት ሥራ ዩኒዬን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ኩማሳ ጉዲና በበኩላቸው የዘርፉ ገበያ በደላሎች የበላይነት መያዝ ለአርሶ አደሩ የገበያ ችግር አንዱና ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በዚህም ምክንያት አርሶ አደሩ ከምርቱ ተገቢውን ዋጋ ሳያገኝ በርካሽ በመሸጥ ለኪሳራ እየተዳረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በዘርፉ የሚታየውን የገበያ ችግር ለመፍታት ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ የምርት ጥራት የማስጠበቅና ዘላቂ የገበያ ትስስር የመፍጠር ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ''ከአገር ውስጥ በተጨማሪ ለሶማሊ ላንድና ለጂቡቲ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት በማቅረብ የአርሶ አደሮችን ምርት ገበያ እንዲያገኝና ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሰራን እንገኛለን'' ብለዋል። ''ዩኒዬኑ የሽንኩርት፣ ቲማቲምና ሌሎች የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ማቀናባበሪያ ፋብሪካ እየገነባን ነው ይህም በምርቱ ላይ እሴት ጨምረን አርሶ አደሩ ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆን ያስችላል'' ብለዋል። የክልሉ የህብረት ሥራ ማህበራት ማስፋፊያ ኤጄንሲ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ መሰረት አሰፋ በበኩላቸው የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት በየጊዜው በሚያጋጥመው የገበያ መዋዠቅ  አርሶ አደሩ ተገቢውን ጥቅም እንዳያገኝ እያደረገ ነው፡፡ ''በኦሮሚያ ክልል በመስኖ ከሚለማው መሬት በዓመት ከ177  ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እየተሰበሰበ ቢሆንም ምርቱ በሚያጋጥመው የገበያ ችግር ተገቢው ጥቅም እየተገኘበት አይደለም'' ብለዋል። የክልሉ መንግስት ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የዩኒዬኖችን አቅም በመገንባትና በማቀናጀት በተደራጀ መልኩ የአርሶ አደሩን  የገበያ  ትስስር መፍጠር እንዲችሉ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል። አርሶ አደሮቹ በምርት ጥራት ላይ በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩ ማድረግና ለምርቱ ከሀገር ውስጥ ባለፈ በውጭ ሀገር ገበያ የማፈላለግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል። በዚህም የመቂ ባቱ፣ጋለማ፣ ሎዴ ሄጦሳና ዶዶላ ዩኒዬኖች ለአምራች አርሶ አደሮች የገበያ ትስስር ለመፍጠር እያደረጉ ያሉት ጥረት አበረታች ቢሆንም ሁሉንም ባሳተፈ መልኩ ችግሩን መፍታት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም