ምእራባውያን መስራት የሚጠበቅባቸውን ባለመስራታቸው ወደ ተሳሳተ የፖሊሲ እርምጃ እንዲያመሩ አድርጓቸዋል- የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተንታኝ ሲሞ ፔካ ፓርቪያነን

52

ምእራባውያን መስራት የሚጠበቅባቸውን ባለመስራታቸው ወደ ተሳሳተ የፖሊሲ እርምጃ እንዲያመሩ አድርጓቸዋል ሲሉ የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተንታኝ ሲሞ ፔካ ፓርቪያነን ተናገሩ።

ፊንላንዳዊው የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተንታኝ ሲሞ ፔካ ፓርቪያነን “Tigray Conflict: Homework Not Done by Western Countries Has Led to Wrong Policy Action“ በሚል ርዕስ ሰሞኑን ባስነበቡት ዘለግ ያለ ጽሑፍ በትግራይ ክልል ስለተካሄደው ህግ የማስከበር እርምጃ የምእራባውያን መገናኛ ብዙሃን፣ መንግስታዊ የልሆኑ ድርጅቶች እና የፖሊሲ አውጭዎች የህወሓትን ፕሮፖጋንዳ በማስተጋባታቸው ምእራባውኑ ታሪካዊ ዳራውን ዘንግተው የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል ሲሉ ገልጸዋል። 

“ግጭቶች በአጋጣሚ አይከሰቱም የሆነ አካል ይጀምራቸዋል እንጂ“ በማለት ሃሳባቸውን የሚያብራሩት  ተንታኙ ሲሞ ፔካ የህወሃት ታጣቂ ቡድን እ.ኤ.አ በ1991 የደርግን ስርዓት አስወግዶ ስልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላ በሀገሪቱ ምርጫ ሲካሄድ የቆየ ቢሆንም አንዳቸውም ነፃና ገለልተኛ እንዳልነበሩ ይገልጻሉ።

ተንታኙ አሁን ሀገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ከ3 ሺህ ዓመታት በላይ ታሪክ ያላትን ሀገር ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር እንድታደርግ ሂደቱን እየመሩት መሆኑን በጽሁፋቸው አትተዋል፡፡

ከዚሁ ጋር አያይዘው እንደገለጹት የታሪክ ተመራማሪዎች ላለፉት 3 አስርት ዓመታት ሀገሪቱን በበላይነት ሲመራ የነበረው የህወሐት ቡድን ሁሉንም የሰላም አማራጮችን ባለመቀበል ተነጥሎ ወጥቶ ቀድሞ ወደ ነበረበት ጫካ መመለስ ለምን እንደፈለገ መመርመር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ተንታኙ እንደሚሉት የህወሃት ቡድን ለበርካታ ዓመታት ያካበተውን በፖለቲካ መስመር የመታገል ብቃት ተጠቅሞ በጥምረት ውስጥ ሆኖ ዴሞክራሲያዊ ትግል ማድረግ ይችል እንደነበር በመጠቆም፤ ነገር ግን ከዚህ በተቃራኒ እንደ ብዙዎቹ የአፍሪካ አማጽያን ሁሉ የተለመደውን ጫካ የመግባት አማራጭ ደግሞታል በማለት ተችተዋል።

ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገውን ትግል የሚያደናቅፈው የዚህ ዓይነት ኋላቀር አስተሳሰብ ነው ሲሉም አክለው ገልጸዋል።

ነገሮች ያበቃላቸው ልክ ህወሃት ጥቅምት ወር መገባደጃ በትግራይ ለበርካታ ዓመታት የክልሉን ህዝብ ከውጭ ወራሪ ሀይል ሲጠብቅ በነበረው የመከላከያ ሰራዊት ላይ በገዛ ጓዶቻቸው እና ወታደራዊ መሪዎቻቸው አመራር ሰጪነት በተኙበት ጥቃት በፈጸሙበት ወቅት ነው የሚሉት ተንታኙ ጥቃት የተፈጸመባቸው የሰራዊቱ አባላት ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ እንደመሆናቸው ሰራዊቱ በተኛበት የተፈጸመበት ከባድ ጥቃት የጭካኔው ማሳያ ነው ብለዋል።

ይህ አስደንጋጭ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ በፍጥነት ተሰራጭቶ ለዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ አጀንዳ መሆኑን አመልክተው፤ በዚህ መካከል የተሰራጩ ፕሮፖጋንዳዎች የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ባለው ጉዳይ ላይ ትክክለኛ ዕውቀትና መረጃ እንዳይኖረው አድርጓል ብለዋል።

ህወሃት ገና ከጅምሩ ስውር አካሄድ በመሄድ የተካነ መሆኑን የሚገልጹት ጸሐፊው በረሃ በነበረበት ወቅት አምባገነኑን ስርዓት ለመገርሰስና ስልጣን ላይ ለመቆናጠጥ የሚያስችለውን የተለያዩ ስልቶችን ይጠቀም እንደነበር የገለጹት ጸሐፊው ምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ምሁራን ጭምር በፕሮፖጋንዳው አጥምቋቸዋል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚገኙ የትግራይ ተወላጆችን በመጠቀም በማህበራዊ ሚዲያ በኩል የሀሰት ወሬዎችን እንዲቀባበሉ በማድረግ በፕሮፓጋንዳ መሳሪያነት ሲጠቀምባቸው እንደቆየ አውስተዋል፡፡

ተንታኙ ለአብነት የሚያነሱት “ህወሓት በትግራይ ህዝብ ላይ የዘር ማጽዳት ዘመቻ ተከፍቶበታል” በሚል ያሰራጨው መረጃ በሰዎች አእምሮ ወዲያው ሩዋንዳን እንዲያስታውሱ የማድረግ ሀይል እንደነበረው አብራርተዋል።

  በትግራይ ህዝብ ላይ የዘር ማጽዳት ዘመቻ  እንደተከፈተበት ያስተጋቡት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ የህወሓት አባላት ናቸው የሚሉት ጸሐፊው እንደ ማሳያ ያቀረቡት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖምን ሲሆን እርሳቸውም በዓለም ላይ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እያስከተለ ያለውን ጉዳት እንዲቀንስ ትኩረት ሰጥተው መስራት ሲገባቸው አሁን ላይ ግን ቀን ከሌት የህወሃትን ፕሮፖጋንዳ ለዓለም ህዝብ በማሰራጨት ተጠምደው ያሉ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

ይህ ቡድን የጦር መሳሪያዎቹን ለመቆጣጠር የሄደበት መንገድ ከወታደራዊ ሳይንስ እይታ አንጻር የተሳሳተ እንደነበር ያነሱት ጸሀፊው ነገር ግን ህወሃት እንዳቀደው የጦር መሳሪዎች መቆጣጠር ቢችል ኖሮ ከድርጅቱ የቆየ እንደእባብ ድንገተኛ የመናደፍ ባህሪው ጋር ተደምሮ በአዲስ አበባ እና በመቀሌ መካከል እጅግ የተካረረ ውጥረት ይነግስ እንደነበር ከዛም እልፍ ሲል በቀጠናው ላይ ሊፈጥር የሚችለውን ችግር ታሳቢ በማድረግ ኢትዮጵያ የኤርትራን ድጋፍ መጠየቋ እና ኤርትራም ፈጣን ምላሽ መስጠቷ ትክክል እንደሆነ አንስተዋል፡፡

በዘመናዊው ዓለም ግጭቶች በብዛት የሚከሰቱት በሀገር ውስጥ ባሉ ተዋናዮች አለመስማማት ምክንያት አልፎ አልፎም በቀጥታ በሀገራት መካከል ጣልቃ በመግባት የሚፈጠር መሆኑን የሚናገሩት ጸሐፊው ጣልቃ የሚገቡ ሀገራት የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር ሲሉ ተጨማሪ ችግር ሊፈጥሩ እንደሚችሉ የሚጠበቅ መሆኑን ይገልጻሉ።

ለዚህ ጥሩ ማሳያ በሚል ያቀረቡት የግብጽን እንቅስቃሴ ነው። ምንም እንኳን ግብጽ የአባይ ውሃን አስታካ ወደ አካባቢው የተጠጋች ቢሆንም የህዳሴ ግድብ ግንባታ በታችኞቹ ሀገራት የውሃ አቅርቦት ላይ ጉዳት እንደሚያስከትል የሚያሳይ ምንም አይነት ማስረጃ ሳይኖር በወቅቱ በኢትዮጰያ ውስጥ የተፈጠረውን ክፍተት በመጠቀም ከሱዳን ጋር በማበር በድንበር አካባቢ ወረራ እንዲፈጸም እና በሁለቱ ሀገራት መካከል ውጥረት እንዲፈጠር ማድረጓን አንስተዋል፡፡

ይህን ተቀባይነት የሌለው የግብጽ ፍላጎት አለመቃወም በቀጥታ የሚገናኘው ከመካከለኛው ምስራቅ ጂኦ ፖለቲክስ ጋር መሆኑን አብራረተዋል።

በዚህ ምክንያት የአሜሪካ መንግስት ለግብጽ አምባገነናዊና ወታደራዊ አስተዳደር ድጋፍ የሚደረግለት መሆኑን አንስተዋል። አሜሪካ ይህንን የምታደርገው በመካከለኛው ምስራቅ ያላትን ቦታ ለማስጠበቅና የእስራኤልን ጥቅም ለማስከበር እንደሆነ አብራርተዋል።

ይህ እውነታ በገሃድ እንዲታይ የሚያደርገው የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የህዳሴው ግድብ በሚመለከት ውግንናቸውን ለግብጽ በማድረግ በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫና ለማሳደር ጥረት አድርገው እንደነበር አስታውሰዋል።

አሁንም በአዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ይህ አዝማሚያ የሚታይ መሆኑን የሚያነሱት ጸሐፊው በአሁኑ የአሜሪካ አስተዳደርና በቀድሞው መካከል የአቀራረብ ልዩነት ካልሆነ በስተቀር ዓላማቸው በመካከለኛው ምስራቅ ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አሁን ላይ የአሜሪካ መንግስት የአማራ ሚሊሻ ከትግራይ ክልል እንዲወጣ የሚሰጡት ትእዛዝ በምሳሌነት የሚያነሱት ተንታኙ ይህ ጥያቄ በአሜሪካ ምርጫ ማግስት ተቃውሞ በተቀሰቀሰበት ወቅት የሜሪላንድ ብሔራዊ ጦር ከዋሽንግተን ዲሲ እንዲወጣ ከመጠየቅ ጋር እኩል ተነፃፅሮ የሚታይ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የገለጹትን እንደማጣቀሻ ተጠቅመዋል።

በመሆኑም አሜሪካ ይህን መሰል ጥያቄ ቢቀርብላት እንዴት ታስተናግደዋልች ሲሉ በጥያቄ መልክ አንስተው ይህም የአንድን የነጻና ሉዓላዊት ሀገር መብትን የሚጋፋ ጣልቃ ገብነት ተገቢነት እንደሌለው አብራርተዋል።

የህወሃት ቡድን ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በድንገት በተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች በሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ በተመሳሳይ ሰዓት ጥቃት መሰንዘሩን ያስታወሱት ጸሐፊው በዚህ ትንኮሳ ምክንያት በመቶዎች የሚቆጠሩ የሰራዊቱ አባላት እና ነባር የጦር አመራሮች በተኙበት መገደላቸውን ተከትሎ መንግስት በወሰደው እርምጃ ቡድን ለሽንፈት መዳረጉን ገልጸዋል።

እኤአ ጥቅምት 9 እና 10 በነበሩት ቀናት ውስጥ የህወሃት ደጋፊዎች በማይካድራ በፈጸሙት የዘር ጭፍጨፋ 800 የሚደርሱ ንጹሃን ሰዎች መግደላቸውንና ከዚያም ድንበር አቋርጠው ወደ ሱዳን መሰደዳቸውን ያስታወሱት ጸሃፊው አሁን ላይ የህወሃት ቅሪቶች የሽምቅ ውጊያ መጀመራቸውን አንስተዋል።

በዚህ የሽምቅ ውጊያም የኤሌክትሪክ መስመሮችን ከመቁረጥ አንስቶ የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶችን በማወደም እና የሰብዓዊ ድጋፎችን በማስተጓጎል ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል።

የተወሰኑ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በተለይ በማደግ ላይ የሚገኙ ምዕራባውያን ሀገራት ጦርነት በተካሄደባቸው አካባቢዎች የሰብዓዊ ድጋፍ በአግባቡ እንዲቀርብ ያላቸውን ስጋት በተደጋጋሚ ሲገልጹ መደመጣቸውን ያነሱት ጸሀፊው ነገር ግን በየትኛውም እንዲህ አይነት ችግር በተከሰተባቸው ሉዓላዊ ሀገራት ላይ የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ በሚል ለሚንቀሳቀሱ አካላት በግዛቱ ውስጥ ያልተገደበ የመንቀሳቀስ ዋስትና የሰጠ ሀገር በተግባር የማይገኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም በአንድ በኩል ለድጋፍ ሰጪዎቹ ደህንነት ሲባል በሌላ በኩል በዓለም የተለያዩ ሀገራት እና አካባዎች ቀደም ባሉ ጊዜያት የተስተዋሉ ለሰብዓዊ ድጋፍ በሚል የሚቀርቡ ድጋፎች ለተቃራኒ አካላት ማጠናከሪያነት የማዋል አዝማሚያን ለመከላከል ሲባል መሆኑን አንስተዋል፡፡

በዚህ ረገድ ህወሃት እ.ኤ.አ. ከ1975 እስከ 1991 በነበሩት ዓመታት የደርግ መንግስትን ከስልጣን ለማውረድ ባደረገው የትጥቅ ትግል ወቅትና ባለፉት 3 አስርት ዓመታት የሰብዓዊ ድጋፎችን ለጦር መሳሪያነት የመጠቀም የዳበረ ልምድ ያለው መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

በትግራይ ክልል የተፈጠረው ግጭት እና አሁን በክልሉ የተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ አስመልክቶ የሚሰጡ ውሳኔዎች ወደኋላ የነበረውን ታሪክ ካለመረዳትና ቁልፍ እውነታዎችን ወደጎን ከመተው የሚመነጩ መሆናቸውን የሚያነሱት ጸሐፊው በዚህ የተነሳ ምእራባውያን ጉዳዩን ከመሰረቱ ከማየት ይልቅ በህወሃት የሚቀነባበረውን በሀሰት የተሞላ መረጃ በማየት ብቻ ወደ ተሳሳተ ድምዳሜ ላይ እንዲደርሱ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።

ይህ የምእራባውያን የችኮላ ውሳኔ ኢትዮጵያን ከቻይና እና ከሩሲያ ጋር ትብብር እንድትፈጥር ሁኔታው ሊያስገድዳት እንደሚችልም አክለው ገልጸዋል።

ይህ የዓለም የፖለቲካ አዝማሚያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እኤአ በኤፕሪል 2021 ባደረጋቸው ስብሰባዎች ላይ በግልጽ ተንጸባርቋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ነባራዊ እውነታ በመገናኛ ብዙሃን የሚሰራጨውን መረጃ ብቻ መሰረት በማድረግ መገንዘብ አይቻልም ያሉት ተንታኙ ለማሳያነትም እ.ኤ.አ በጥር 2021 የዋሽንግተን ፖስት ኤዲቶሪያል ኢትዮጵያ ትግራይን እንደወረረች አድርጎ የዘገበውን ማየት በቂ እንደሚሆን ይገልጻሉ።

ተንታኙ እንደሚገልጹት የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ ኢትዮጵያን በተመለከተ አስቀድመው መስራት የነበረባቸውን የቤት ስራ አልሰሩም።

ይህ መሆኑን በግልጽ የሚያሳየው የፖሊሲ ውሳኔ ሰጪዎች በተደጋጋሚ የተኩስ አቁም ጥሪ ሲያቀርቡ መሰንበታቸው እንዲሁም ድርድር እንዲያደርጉ ሲገፋፉ እንደነበር በማነሳት ይተቻሉ። የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ ይህን ጥሪ ማቅረባቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው እውነታ ምን ያህል መዘንጋታቸውን የሚያሳይ ነው በማለትም ያብራራሉ።

ኢትዮጵያ ካበቃለትና በፓርላማ በሽብርተኝነት ከተፈረጀ የህወሃት ቡድን ጋር ድርድር የማድረግ ምንም ዓይነት ፍላጎት የላትም የሚሉት ተንታኙ መንግስት ጉዳዩ የውስጥ መሆኑንና የውጭ ጣልቃ ገብነት ተቀባይነት እንደሌለው በግልጽ ማሳወቁንም አብራርተዋል።

ይህ የመንግስት መልእክት በምእራባውያን ዘንድ ሊከበር ይገባው እንደነበር አያይዘው ገልጸዋል። ይሁን እንጂ አሁን ላይ በምእራባውያን በኩል እየተስተዋለ ያለው ለኢትዮጵያ “እኛ እናውቅላችኋለን” የሚል አባዜ መኖሩን በጽሁፋቸው አስፍረዋል፡፡ 

በመጨረሻ ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ተፈጽመዋል በሚል የሚቀርቡ አቤቱታዎችን ለማጣራት ቁርጠኛ መሆኗን እንዳረጋገጠች ያስታወሱት ተንታኙ በዘመናዊ አስተሳሰብ ይመራል የሚባለው የአውሮፓና የአሜሪካ ጦር እንኳ ከሰብአዊ መብት ጥሰት ሙሉ በሙሉ የጸዳ ነው ሊባል እንደማይችል ኢራቅንና አፍጋኒስታን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።

ስለሆነም ምእራባውያን ሀገራት ራሳቸውን ፍጹም አድርገው የሚያቀርቡትን በመተው አቋማቸውን ቢያስተካክሉ ይመረጣል ሲሉ ገልጸዋል።

ይልቁንም እውነታውን በጥልቀት ተገንዝበው ለኢትዮጵያ አሁናዊ ሁኔታ መፍትሔ ሊሆን የሚችልና ሀገሪቱ እያከናወነች ያለውን ስራ ሊያጠናክር የሚችል ገንቢ ድጋፍ መስጠት ቢችሉ የተሻለ እንደሚሆን ምክረሃሳባቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም