ለአካባቢያቸው ዘላቂ ሠላም የሚጠበቅቸውን እንደሚወጡ የጌዴኦና ጉጂ ዞኖች ወጣቶች ገለጹ

123
ዲላ ሀምሌ 26/2010 የአካባቢያቸውን ዘላቂ ሠላምና የህግ የበላይነት እንዲከበር  የሚጠበቅቸውን እንደሚወጡ በጌዴኦና ጉጂ ዞኖች አስተያየታቸውን የሰጡ ወጣቶች ገለጹ፡፡ በምዕራብና ምስራቅ ጉጂ ዞኖች እንዲሁም በጌዴኦ ዞን አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በጉጂና ጌዴኦ አባ ገዳዎች አማካይነት በቅርቡ የሠላም ጉባኤ ተካሄዷል፡፡ ይህን ተከትሎ የሁለቱ ዞኖች ወጣቶች ለኢዜአ እንዳሉት ለአካባቢያቸው ሰላም አንደነታቸውን አጠናክረው ለመስራት ዝግጁ ናቸው፡፡ በምዕራብ ጉጂ ዞን የቡሌ ሆራ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ዱከሌ አዶላ በሰጠው አስተያየት "ከጌዴኦ ህብረተሰብ ጋር በሥጋና ደም ተዋህደን የኖርን አንድ ህዝቦች ነን" ብሏል ፡፡ ከዚህ በኋላ አብረው ተባብረው በመደጋገፍ መኖራቸወን አንደሚቀጥሉ ጠቅሶ ንብረት በማውደምና በመዝረፍ የወጣቱን ስም የሚያጠፉ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ አመልክቷል ፡፡ ወጣት ዱከሌ በማያያዝም " በአካባቢያችን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና የዜጎች መብት ጥሰት እንዳይኖር  በመከላከል የህግ የበላይነት እንዲከበር የድርሻችንን እንወጣለን " ብሏል፡፡ የዚሁ ወረዳው ነዋሪው ወጣት ዱቤ በቀለ በበኩሉ በፀጥታ ችግር ምክንያት ከቦታ ወደቦታ ለመንቀሳቀስ ሲቸገሩ መቆየታቸወን አስታውሶ "አሁን ግን ሰርተን  የምንገባበት ሁኔታ ተፈጥሯል ፤ የዕርቅ ጉባኤ  በመካሄዱ ደስ ብሎናል" ብሏል ፡፡ የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ በፍቅር እንደሚቀበሏቸው የተናገረው  ወጣት ዱቤ ያላቸውን  በማካፈል የመልሶ ማቋቋሙን ሥራ እንደሚያግዙም ገልጻል ፡፡ በአካባቢያቸው ቄሮ ነን በሚል ተደራጅተው ጥፋት የሚፈጽሙ እንደማይወክሏቸውና ይህንን በማስቆም የህግ የበላይነት እንዲከበር ከሌሎች ወጣቶች ጋር በመሆን እንደሚሰራም አመልክታል ፡፡ በምዕራብ ጉጂ ዞን የቀርጫ ወረዳ ነዋሪ  የጌዴኦ ወጣት ታምራት አበበ በሰጠው አስተያየት "ከጉጂ ህዝብ ጋር ከጥንት ጀምሮ በጋራ ኖረናል" ብሏል፡፡ ተፈጥሮ በነበረው ችግር የተጎዱ መኖሩያ ቤቶችን መልሶ በመገንባት ፤ ጥፋተኞችንም ለሕግ አሳልፎ በመስጠት መንግስት ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚወስደውን እርምጃ ለማጋዝ ዝግጁ መሆኑን ተናግራል፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራ ከ20 ዓመታት በኋላ አንድነት መፍጠራቸው በሁለቱም ህዝቦች ዘንድ ከፍተኛ ደስታ መፍጠሩን ያስታወሰው ወጣት ታምራት " እኛም እርስ በእርስ ተደጋግፈን መኖር ይጠበቅብናል "ብሏል ፡፡ ሌላው  የጌዴኦ ወጣት አስፋው ማርያም በበኩሉ በሁለቱ ህዝቦች መካከል የእርቅ ጉባኤ በመካሄደ መደሰቱን ገለፆ ከአካባቢው ወጣቶች ጋር በመተባበርና በመመካከር አባገዳዎች ለዘላቂ ሠላም የሚደርጉትን ጥረት እንደሚግዝ ገልጿል፡፡ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለስና መልሶ የማቋቋሙ ተግባርም በሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት እንደሚገባም ወጣት አስፋው ጠቅሷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም