በቅርቡ የተከሰተውን ግጭት አብሮነታችንን በማጠናከር አሳልፈነዋል - የአሶሳና አካባቢ ነዋሪዎች

58
አሶሳ ሀምሌ 26/2010 በአሶሳ ከተማና አካባቢዋ ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ወቅት የተለያዩ ብሄር ተወላጆች አንዱ በሌላው ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ያደረጉት ጥበቃ የአብሮነታቸው ማሳያ መሆኑን የከተማዋና አካባቢዋ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ ችግሩ በተከሰተበት ወቅት የተለያዩ ብሄረሰብ ተወላጅ የሆኑ ነዋሪዎች በአንድነት መቆማቸው እንዲሁም በሌሎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ መከላከላቸው ሊደርስ የሚችለውን ከፍተኛ ጉዳት እንዲቀንስ ማድረጉን ኢዜአ ያነጋራቸው ነዋሪዎች ገልፀዋል፡፡ የአሶሳ ከተማን ጨምሮ በተወሰኑ ወረዳዎች ከአንድ ወር በፊት ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር በሰው ህይወትና አካል ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል፡፡ በአሶሳ ከተማ ተወልደው ማደጋቸውን የተናገሩት ወጣት የሱፍ ሰይድና ጓደኞቹ ግጭቱ በተከሰተበት ወቅት የብሄር ማንነታቸው ሳይለያያቸው በህብረት በመቆም  እርስ በርስ በመጠባበቅ በወቀቱ በማናቸውም ላይ ጉዳት አለመድረሱን አስታውቀዋል፡፡ ወጣቶቹ ብሄርን መሰረት ያደረጉ ልዩነቶች የግጭት መነሻ ሊሆን አይችልም ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የተናገሩትን በመግለፅ እንደዚህ አይነት ግጭቶችን በመፍጠር ለማትረፍ ማሰብ ጊዜው ያለፈበት ፋሽን እንደሆነም ተረድተናል ብለዋል። በአሶሳ አቅራቢያ በምትገኘው ጋምቤላ ቀበሌ ከሰባት አመት በላይ መኖራቸውን የገለፁት አቶ ተመስገን ኩሳ ደግሞ በቀበሌው ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግር በአካባቢው የሚኖሩ እናቶችና የአገር ሽማግሌዎች ጉዳት እንዳይደርስባቸው እንደጠበቋቸው ገልፀዋል፡፡ ችግሩን የፈጠሩ አካላት ወጣቶችን በማሳሳት አደጋ  ለመፍጠር ቢሞክሩም ሰላም ፈላጊ የሆኑ ነዋሪዎች ባደረጉት ጥረት ጉዳት መቀነሱን ጠቁመው ለዚህም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በዚህ ቀበሌ ናሪና የአገር ሽማግሌው አቶ አህመድ ያሲን በበኩላቸው ለዓመታት ክፉና ደጉን አብረው ያሳለፋ ጎረቤቶቻቸው ላይ ጉዳት ከሚደርስ  ራሳቸው አሳልፉው በመስጠት መከላከልን መምረጣቸውን ገልፀዋል፡፡ በወቅቱም በአካባቢያቸው የሚኖሩ ግለሰቦች ደህንነታቸው ተጠብቆ ከአካባቢው እንዲወጡ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡ በክልሉ አስተደደርና ፀጥታ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ የግጭት መከላከልና አፈታት ዳይሬክተር አቶ ኮማንደር ወርቁ በከተማዋና የተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው ችግር በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ሊያደናቅፋ የሚፈልጉ  አካላት ተግባር እንደነበር አስታወሰዋል። ችግሩ በተፈጠረበት ወቅት የተለያየ ብሄረሰብ ተወላጅ የሆኑ ወገኖች አንዱ በሌላው ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ሲጠበቁ የነበሩ ነዋሪዎች እንደነበሩም ገልፀዋል፡፡ የተፈጠረው ችግር ህዝባዊ መሰረት የሌለው ለመሆኑም ማሳያ ነው ያሉት ኮማንደሩ ከችግሩ በኋላም በተካሄዱ ውይይቶች በህዝብ መካከል የተፈጠረ ፀብ እንደሌለና አጥፊዎች እንዲጠየቁ ህዝቡ መጠየቁን አስታውሰዋል፡፡ የክልሉ መንግስትም ከችግሩ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በህግ ጉዳያቸው እንዲታይ እያደረገ እንደሚገኝና የማጣራቱ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም