የመጽሐፍ ዓውደ ርዕይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተሰሩ የምርምር ሥራዎችን ወደ ተግባር ለመቀየር ይረዳል

72
አዲስ አበባ ሀምሌ 26/2010 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በ‘ንባብ ለህይወት የመጽሐፍ ዓውደ ርዕይ' ላይ መሳተፋቸው በዩኒቨርሲቲዎች የተሰሩ የምርምር ውጤቶችን ወደ ተግባር ለመቀየር እንደሚረዳ በዓውደ ርዕዩ ላይ የተሳተፉ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ተናገሩ። 4ኛው ንባብ ለህይወት የመጽሐፍ ዓውደ ርእይ ዛሬ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ተከፈተ። በአውደ ርዕዩ ላይ የተሳተፉት የጎንደርና የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ መምህራን በተለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት ዓውደ ርዕዩ በዩኒቨርሲቲዎች እየተሰሩ ያሉ የምርምር ውጤቶችን ለማስተዋወቅ የሚረዳ ነው። በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኢንደስትሪ ትስስርና ሽግግር ዳይሬክተር ኢንጂነር ሰለሞን መስፍን እንዳሉት ዓውደ ርዕዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ሥራዎች ለማህበረሰቡ ከማስተዋወቅ በተጨማሪ የምርምር ውጤቶችን ወደ ምርት በመቀየር ተደራሽ የሚያደርጉ ኢንደስትሪዎች  እንደሚፈጥርም ገልጸዋል። የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ቋንቋ መምህር አቶ ሸዋ ባሲዘው በበኩላቸው በዓውደ ርዕዩ መሳተፋቸው ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ትስስር ለመፍጠር እንደሚረዳቸው ገልጸዋል። "በንባብ ያልዳበረ ዜጋ ኀብረተሰቡን ማገልገል አይችልም" ያሉት መምህር ሸዋ፤ እንዲህ ዓይነት ፕሮግራም በሀገር አቀፍ ደረጃ መዘጋጀቱ የንባብ ባህልን በማሳደግ ብቁ ዜጋን ለመፍጠር እንደሚያስችል ገልጸዋል። የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት መምህር አቤኔዘር እስጢፋኖስ በበኩላቸው ዓውደ ርዕዩ ዩኒቨርሲቲዎች በማኀብረሰብ አቀፍ አገልግሎት ምን እየሰሩ እንደሆነ ለማሳየትና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ የሚረዳ  ነው ብለዋል። በ4ኛው ንባብ ለህይወት የመጽሐፍ ዓውደ ርዕይ ላይ አስር ዩኒቨርሲቲዎቸ ተሳታፊ ሆነዋል። የመጽሐፍ ዓውደ ርዕዩ "ኢትዮጵያን በመፃህፍት" በሚል መሪ ሐሳብ እስከ ሐምሌ 30 ድረስ በነፃ ለህዝብ ክፍት ሆኖ ይቆያል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም