ለዘላቂ ልማትና ሰላም አርአያ ሆነው እንደሚሰሩ በመቀሌ የወጣቶች ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች ገለጹ

60
መቀሌ ግንቦት 7/2010 ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥና ሰላምን አጠናክሮ ለማስቀጠል አርአያ ሆነው እንደሚሰሩ በመቀሌ ከተማ እየተካሄደ ባለው የወጣቶች ኮንፈረንስ ላይ እየተሳተፉ ያሉ ወጣቶች ገለጹ፡፡ በመቀሌ ሰማዕታት አዳራሽ በተዘጋጀውና ከ600 በላይ ወጣቶች ተሳታፊ የሆኑበት የሰላምና የልማት ኮንፈረንስ ውይይት ዛሬም ቀጥሎ ውሏል፡፡ የኮንፍረንሱ ተሳታፊ ወጣት ኪሮስ ገብረጻድቃን እንደገለጸው ወጣቶች የተረጋጋ ሰላም ለማስፈንና ፈጣን ልማት ለማምጣት ከማንም በላይ ወጣቱ አርአያ መሆን እንዳለበት ገልጾ ለዚህም መዘጋጀቱን ተናግሯል፡፡ በክልሉ ለትምህርት ተደራሽነት የተሰጠውን ትኩረት ያህል ወጣቶች ታሪካቸው እንዲያውቁና ስነ ምግባራቸው የተጠበቀ እንዲሆን ተገቢ ትኩረት ሳይሰጠው መቆየቱን ጠቁሟል፡፡ ለዚህ የወጣቱ ደርሻ ያለ ቢሆንም በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና ምሁራን የተጣለባቸው ኃላፊነት በአግባቡ አለመወጣታቸው ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ተናግሯል፡፡ በቀጣይ የአገሩንና የቀደምት አባቶቹን ታሪክ በማወቅ ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ፈጣን ልማትን አጠናክሮ ለማስቀጠል በሚደረገው አገራዊ ጥረት ግንባር ቀደም ሆኖ ለመንቀሳቀስ መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡ ኮንፈረንሱ በመንግስትና በወጣቶች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን የለየና ቀጣይ የሥራ አቅጣጫ ለማስቀመጥ የሚያስቸል መሆኑን የተናገረችው ሌላዋ የኮንፍረንሱ ተሳታፊ ወጣት ኤልሳ ስብሃት ናት። አገሪቱ የተሻለ የዕድገት ደረጃ ላይ ስትደርስ ወጣቱም የተሻለ ሕይወት እንደሚኖረው በኮንፍረንሱ የጋራ መግባባት ላይ መድረሱን የገለጸችው ወጣቷ፣ ሰላምን ለማስጠበቅና ልማጥትን ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት ግንባር ቀደም ሆና እንደምትንቀሳቀስ ተናግራለች፡፡ ከአዲስ አባባ አስተዳደር የተወከለው ወጣት ሰሎሞን ኃይሉ በበኩሉ መልካም አስተዳደር አለመስፈንና ሙስና ወጣቱን ተጠቃሚ እንዳይሆን እንቅፋት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህን ችግር ለመወጣት የወጣቱን  ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ በኮንፍረንሱ የጋራ ድምዳሜ ላይ የተደረሰ መሆኑን አስረድቷል፡፡ "ወጣቱ አሁን እያጋጠሙ ያሉትን ችግሮች ለመወጣት በተደራጀ አግባብ መንቀሳቀስ ይገባል" ሲልም ገልጿል፡፡ የክልሉ ምክትል ርዕሰመስተዳደር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ከወጣቶቹ ጋር በተወያዩበት ወቅተ እንዳሉት፣ የክልሉን ህዝብ ከድህነትና ኋላ ቀርነት ለማላቀቅ በክልሉ መንግስት በኩል ትኩረት እንደሚሰጥ አመልክተዋል። "ወጣቱም በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ልማትን ለማፋጠን ከሚያደርገው ጥረት በሻገር ለህዝቦች አንድናትና አብሮነት ተገቢ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል" ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም