ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶችን ለማስወገድ የዘመናዊ መሳሪያዎች ተከላ ሊጀመር ነው

1403

አዲስ አበባ ሀምሌ 26/2010ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶችን ከማስወገድ ጋር በተያያዘ የነበሩ ችግሮችን ይፈታሉ ተብለው የታመነባቸው ዘመናዊ የማቃጠያ መሳሪያዎች ተከላ ሊጀመር እንደሆነ የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ አስታወቀ።

መሣሪያዎቹ በ16 ሚሊዮን ዶላር ወጪ መገዛታቸውን ኤጀንሲው ገልጿል።

ከግሎባል ፈንድ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የተገዙት ስምንት መሳሪያዎች በአዳማ፣ በነቀምት፣ በጅማ፣ በድሬዳዋ፣ በሐዋሳ፣ በመቀሌ፣ በደሴና በባህርዳር ከተሞች በተመረጡ ቦታዎች ከነሐሴ ወር 2010 ዓ ም ጀምሮ የተከላው ሥራ እንደሚጀመር ኤጀንሲው ገልጿል።

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዓለም አድራሮ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከዚህ ቀደም ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶች የሚወገዱት ጉድጓድ ውስጥ በመቅበር አልያም ምቹ ባልሆነ ቦታ በማቃጠል በመሆኑ መድኃኒቶቹ በሚወገዱበት አካባቢ በሚኖሩ ሰዎች ላይ የጎንዮሽ የጤና ጉዳት እያስከተለና አካባቢውም ለብክለት እየተጋለጠ ቆይቷል።

በአሁኑ ወቅት በኤጀንሲው የመድኃኒት ማከማቻ መጋዘኖችና በተለያዩ የጤና ተቋማት በርካታ ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶች እንደተከማቹ የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ መድኃኒቶቹን ለማስወገድ የዘመናዊ መሣሪያ ግዢ መፈጸሙን ጠቁመዋል።

መሳሪያው በሰዓት አንድ ሺህ ኪሎ ግራም መድኃኒት የማቃጠል አቅም እንዳለው አቶ ተስፋዓለም ተናግረዋል።

የመሣሪያዎቹ ተከላ በሁለት ዙር ተከፋፍሎ የሚከናወን እንደሆነ የጠቆሙት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ የመጀመሪያ ዙር ተከላ በነሐሴ ወር በአዳማ፣ በሐዋሳና በባህርዳር ከተሞች እንደሚከናወን አስረድተዋል።

በሁለተኛው ዙር ከመስከረም እስከ ህዳር 2011 ዓ ም ድረስ  በነቀምት፣ በጅማ፣ በድሬዳዋ፣ በመቐለና በደሴ ከተሞች የሚከናወን መሆኑን ጠቁመዋል።

መሣሪያዎቹ አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የጎንዮሽ የጤና ጉዳትና የአካባቢ ብክለት የማያስከትሉ መሆኑን ኤጀንሲው በጥናት ማረጋገጡን የገለጹት አቶ ተስፋዓለም ከዚህ በፊት በመድኃኒት አወጋገድ ዙሪያ የሚከሰቱ ችግሮችን ሙሉ በሙሉ የሚያስወግድ እንደሆነም አክለዋል።