በሀገሪቱ ሰፊ የስራ እድል ለማመቻቸት ርብርብ እየተደረገ ነው

122

ሀዋሳ ፣ ግንቦት 13 /2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ልትሸከም የምትችለውን ኢኮኖሚ መሠረት ያደረገ ሰፊ የስራ እድል ለዜጎች ለማመቻቸት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የፌዴራል ሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን አስታወቀ።

የፌዴራልና የክልል ሥራ ዕድል ፈጠራ አካላት የተሳተፉበት የበጀት ዓመቱ የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም እና የመረጃ ጥራት ዳሰሳ ጥናት ግምገማ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተጀምሯል።

በመድረኩ የፌዴራል ሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽነር አቶ ንጉሱ ጥላሁን እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ እምቅ ሀብት ከአካባቢ አካባቢ፣ ከክልል ክልል፣ ከዘርፍ ዘርፍ መለያየትን በማድረግ የወጣውን ዕቅድ ክልሎች እንዲፈጽሙ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ ነው።

በተለይ በስራ እድል ፈጠራ መስክ የተለያዩ የማሻሻያ እርምጃዎች በመንግሥት መወሰዱን አስረድተው፤ እንደማያሰሩ በጥናት የተለዩ መመሪያዎችና ደንቦች ላይ ፍተሻ መደረጉን ገልጸዋል።

ለዘመናት የቆየውን የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ስትራቴጂን የመከለስ ስራ መጠናቀቁን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በርካታ አዳዲስ ሀሳብና እውቀት ያላቸው ስራ ፈጣሪዎችን ጥያቄ በቀላሉ ለማስተናገድ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ጀማሪ ኢንተርፕራይዞችን ወደ ስራ የሚያስገባ ረቂቅ አዋጅ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ከፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና ገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።

"ለዜጎች የስራ እድል ከምንፈጥርባቸው አማራጮች መካከል የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ነው" ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ለዚህ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

እነዚህንና ሌሎችንም አዳዲስ አሰራሮች ስራ ላይ በማዋል ሀገሪቱ ልትሸከም የምትችለውን ኢኮኖሚ መሠረት ያደረገ ሰፊ የስራ እድል ለማመቻቸት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ ባለፈው ዓመት ያጋጠመው ተጽዕኖ ዘንድሮ እንዳይደገም በተሰራ ስራ በርካታ ኢንተርፕራይዞችን ከመበተን ማዳን መቻሉን ተናግረዋል።

እንደ አቶ ንጉሱ ገለፃ፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተደረገ ጥረት ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ተችሏል።

በኮሚሽኑ የክትትልና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ማናጀር አቶ እውነቱ ፈለቀ በበኩላቸው፤ በበጀት ዓመቱ 45 ሺህ 629 ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተው ስራ ውስጥ ለገቡ አንቀሳቃሾች 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ብድር መሰራጨቱን ገልጸዋል።

እንቅስቃሴያቸው ውጤታማ እንዲሆንም ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር በየደረጃው በማመቻቸት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም