በድሬዳዋ በገጠር ቀበሌዎች ለተደራጁ ስራ አጥ ወጣቶች አምስት የእርሻ ትራክተሮች በድጋፍ ተበረከተላቸው

131

ድሬዳዋ ፣ግንቦት 13/2013(ኢዜአ) የድሬዳዋ አስተዳደር በገጠር ቀበሌዎች በማህበር ለተደራጁ ስራ አጥ ወጣቶች በ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የተገዙ የእርሻ ትራክተሮችን በድጋፍ አበረከተ።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር በአስተዳደሩ የተገዙ የአምስት የእርሻ ትራክተሮችን ቁልፍ ዛሬ ለወጣቶቹ አበርክተዋል።

ትራክተሮቹ በድጋፍ የተበረከቱት በአምስት ገጠር ቀበሌዎች ከ80 በላይ አባላት ላሏቸው አምስት የወጣት ማህበራት ነው።

የቢሮ ሀላፊው በወቅቱ እንደገለጹት ትራክተሮቹ በገጠር የወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ከተመደበ በጀት ውስጥ 5 ሚሊዮን 237 ሺህ ብር የተገዙ ናቸው።

በአስተዳደሩ ገጠር ቀበሌዎች የህብረተሰቡን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግና ለወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

አስተዳደሩ ለገጠሩ ወጣቶች ትኩረት በመስጠት በተለይ ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ በየመስኩ የስራ ዕድል እንዲያገኙ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የገጠሩን ህብረተሰብ በአነስተኛ የእርሻ መሬት ላይ የመስኖ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚደረጉ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ ትራክተሮች የራሳቸው አስተዋጽኦ እንዳላቸው የገለፁት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር የግብርና፣ ዉሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ናቸው።

ትራክተሮቹ የአርሶአደሩን ማሳ በአነስተኛ ክፍያ በፍጥነትና በዘመናዊ መንገድ በማረስ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ያግዛሉ” ብለዋል።

ትራክተር ከተሰጣቸው ወጣት ማህበራት መካከል የገርበ አነኖ ገጠር ወጣቶች ማህበር ተወካይ ወጣት ኒማአሌ አሊ “በማህበር የተደራጀን 20 ወጣቶች በተፈጠረልን ስራ ተጠቅመን እራሳችንን በመለወጥ ለሌሎች ምሳሌ ለመሆን ተዘጋጅተናል “ ብሏል። 

“ስለ ትራክተር አጠቃቀም አስፈላጊው ስልጠና ተሰጥቶናል፤ ሃብቱን በጥንቃቄ በመያዝ ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጥ እናደርጋለን” ሲል ወጣቱ ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም