ሚኒስቴሩ የወጣቶችን የንባብ ባህል ለማሳደግ ከሚሰሩ ተቋማት ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ገለፀ

66
አዲስ አበባ ሀምሌ 26/2010 የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የወጣቶችን የንባብ ባህል ለማሳደግ ከሚሰሩ ተቋማት ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ገለፀ። 4ኛው ንባብ ለህይወት የመጽሐፍ ዓውደ ርእይ በኢግዚቢሽን ማዕከል ተከፍቷል። የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬህይወት አያሌው በዚሁ ወቅት እንዳሉት ወጣቶች ችግር ፈቺ እንዲሆኑ በእውቀት፣ በክህሎትና በመልካም ስብዕና እንዲታነፁ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይጠይቃል። "መልካም አስተሳሰብ የተላበሰ፣ ምክንያታዊና በስራ የሚያምን ትውልድ ለመፍጠር ንባብ ትልቅ ድርሻ አለው" ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ሁሉም የወጣቶችን የንባብ ባህል ለማሳደግ መሰራት አለበት ብለዋል። ባለፉት ዓመታት የኀብረተሰቡን የንባብ ባህል ለማሳደግ እየሰራ ያለውን ‘ንባብ ለህይወት ኢትዮጵያን'ም አመስግነዋል። ሚኒስቴሩ ወጣቶች ከአልባሌ ቦታዎች ተቆጥበው የእረፍት ጊዜያቸውን በንባብ እንዲያሳልፉ ለማድረግ ከሚሰሩ ተቋማት ጋር በመተባበር  ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም ገልፀዋል። የ‘ንባብ ለህይወት ኢትዮጵያ ፕሮጀክት' ኃላፊ አቶ ቢኒያም ከበደ በዓውደ ርዕዩ ላይ የክልል ዩኒቨርሲቲዎች የጥናት ውጤት ይዘው መቅረባቸው የዘንድሮውን ዓውደ ርዕይ የተለየ ያደርገዋል ብለዋል። ዓውደ ርዕዩን ሀገር አቀፍ ለማድረግ ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር መወያየታቸውንም ነው የገለፁት። በዓውደ ርዕዩ የመፅሀፍ ምረቃ እንደሚኖርና የተለያዩ መጻህፍት በቅናሽ ዋጋ እንደሚቀርቡ የገለጹት የፕሮጀክቱ ኃላፊ ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ውጤቶችን ለኀብረተሰቡ እንደሚያቀርቡና የተለያዩ ኪነ-ጥበባዊ ዝግጅቶችም እንደሚኖሩ አብራርተዋል። በዓውደ ርዕዩ መዝጊያ ቀን የወርቅ ብዕር ተሸላሚ የሚሆነው ሰውም ይፋ እንደሚሆን ነው የተገለፀው። ከዛሬ ሐምሌ 26 ጀምሮ እስከ ሐምሌ 30 በሚቆየው ዓውደ ርዕይ ላይ 200 በላይ ተሳታፊዎች እንዳሉና በርካታ ሰዎች እንደሚጎበኙትም ነው የተነገረው።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም