የዜጎችን ሰብአዊ መብት በማክበርና በማስከበር ረገድ መገናኛ ብዙሃን ቁልፍ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ ተገለፀ

61
አዳማ ሀምሌ 26/2010 የዜጎችን ሰብአዊ መብት በማክበርና በማስከበር ረገድ መገናኛ ብዙሃን ቁልፍ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር አስገነዘቡ። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንና የመገናኛ ብዙሃን ፎረም ምስረታ መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ ተካሄዷል። ዋና ኮሚሽነሩ ዶክተር አዲሱ ገብረእግዚአብሔር በወቅቱ  ለኢዜአ እንዳስታወቁት ሰብአዊ መብት ማስከበር የኮሚሽኑና የዴሞክራሲ ተቋማት ተልዕኮ ብቻ አይደለም። ይልቁን በየደረጃው የሚገኙ ምክር ቤቶች፣ የአስፈጻሚ አካላትና የአገር ተልእኮ ስለሆነ በሕገ መንግስቱ የተረጋገጠው ሰብአዊ መብት ሳይሸራረፍ እንዲከበር ለማድረግ ሚዲያ ቁልፍ ሚና እንዳለው ገልጸዋል። ስለ ህገ መንግስትና ሰብአዊ መብት አስተምህሮት፣ ስለ ዜጎች መብትና ግዴታ ከማሳወቅ አኳያ ሚዲያ የማይተካ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ኮሚሽኑ በእውቀት ላይ የተመሰረተና ያልተዛባ መልዕእክት ለማስተላለፍ የሚያስችል መመሪያ አዘጋጅቷል ያሉት ዶክተር አዲሱ በቀጣይም ከሚዲያ ተቋማት ጋር እጅና ጓንት ሆነን በመስራት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የፎረሙ መመስራት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡ ኮሚሽኑ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ የሚያጋጥሙ ግጭቶች፣ ሁከትና ብጥብጥ በሚገባ በመመርመር ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እያቀረበ መሆኑንም ጠቅሰዋል። ባለፉት ሁለት ዓመታት በኦሮሚያ፣ አማራና በደቡብ ክልሎች የነበረውን ግጭት በማስመልከት ኮሚሽኑ ያካሄደውን ማጣራት ከሚያዛላቅ ምክረ ሀሳብ ጭምር ለምክር ቤት በማቅረብ ተጠያቂነትና የህግ የበላይነት እንዲከበር መስራቱን አስታውቀዋል። እየተከሰቱ ያሉት ገጭቶች መሰረታዊ መንስኤ እንዳላቸው ገልጸው መንግስት ኮሚሽኑ የሚሰጠውን ምክረ ሀሳብ በጥንቃቄ በመጠቀም ለግጭቶች መንስኤ የሆኑትን ጉዳዮች ሊፈታ ይገባል። ''የፍትህ ጥያቄዎች መልስ እያገኙ ሲሄዱ ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት እንደምንችል ኮሚሽኑ ያካሄደው ጥናትና ምርምር ያስረዳል'' ብለዋል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር አቶ እሸት ገብሬ በበኩላቸው ''በሀገሪቱ ከሰብአዊ መብቶች ሁሉ ልዩ ትኩረት የሚሰጣቸው  በህይወት የመኖር መብት፣ የመዘዋወር ነጻነትና ፍትህ የማግኘት መብት አደጋ ላይ ወድቀዋል'' ብለዋል። በመሆኑም የሚዲያ ተቋማትና ባለሙያዎች በኢዲቶሪያል ፖሊሲ ውስጥ ስለሰብአዊ መብት አያያዝ ትኩረት በመስጠት እነዚህ መብቶች በሁሉም ዘንድ እንዲከበሩ አጀንዳ አድርገው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል። ለመብት ጥሰት ተጋላጭ ለሆኑ ሴቶች፣ ህፃናትና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ህገ መንግስታዊ መብቶችና ነፃነቶች መከበራቸውን በውል ማረጋገጥ የሚዲያው ተልእኮ እንዲሆን ጠይቀዋል። የመድረኩ ተሳታፊና ጋዜጠኛ ትዕግስቱ በቀለ በሰጠው አስተያየት የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ተቋማትና ኮሚሽኑ በጋራ መስራታቸው ለዜጎች ልእልና መከበር፣ ለሀገር ሰላም፣ ብልጽግና እና ለህዝቦች አንድነት የላቀ አስተዋዕኦ ይኖረዋል የሚል እምነት አለው። በሰብአዊ መብት ዙሪያ ሚዲያው ምንም አልሰራም የሚለው ጋዜጠኛ ተዕግስቱ ለማይመለከተው ለአውሮፓ እግር ኳስ ክለብ የሀገራችን ሚዲያ የሰራውን ያህል እንኳን አልተቀሳቀሰም ባይ ነው። በቀጣይ በቁጭት መንፈስ በመነሳሳት ለሀገራችን ውድቀትና ትንሳኤ የሆኑት ጉዳዮች በግልጽ በማውጣት ማህበራዊ ኃላፊነታችንን እንወጣ ይላል። ለአንድ ቀን በተዘጋጀው የፎረሙ ምስረታ ላይ ከመንግስትና ከግል ሚዲያ ተቋማት የተውጣጡ ጋዜጠኞችና የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም