በአፋር ክልል ለሚሰጠው ክልላዊና ብሄራዊ ፈተና ዝግጅት መደረጉ ተገለፀ

69
ሰመራ ግንቦት 7/2010 በአፋር ክልል የዘንድሮው ክልላዊና ብሄራዊ ፈተና በስኬት እንዲጠናቀቅ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን የትምህርትና የጸጥታ አካላት አመራሮች ገለጹ፡ የክልሉ ትምህር ቢሮ ትናንት በሰመራ ከተማ ባዘጋጀው የአንድ ቀን የምክክር መድረክ ላይ የተሳተፉ ጸጥታና የትምህርት አመራሮች እንደገለጹት ከግንቦት ወር 2010 መጨረሻ ጀምሮ እስከ ሰኔ አጋማሽ የሚሰጠው ክልላዊና ብሄራዊ ፈተና በስኬት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል፡፡ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ መሃመድ ኡዳ እንደተናገሩት በክልል ዘንድሮ ከ21ሺ በላይ ተማሪዎች ክልላዊና ብሄራዊ ፈተና ይወስዳሉ። ኩረጃን ጨምሮ የፈተና ሂደቱን የሚያውኩ ህገወጥ ተግባራትን ለማስቆም የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ከፈተና ስርጪቱ እስከ ፈተና ሂደቱ ድረስ ያለምንም እንከን ለማከናወን ከክልሉ ፀጥታና አስተዳደር ጉዳዮች ቢሮ ጋር በመቀናጀት አደረጃጀቶች ተፈጠረው አሰፈላጊው ቅድመ-ዝግጅ መደረጉን አስረድተዋል። የክልሉ ጸጥታና አስተዳደር ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን አኒሳ በበኩላቸው በፈተና ወቅት የሚያገጥሙ ህገወጥ ተግባራትን ለመከላከል የፀጥታ አካሉ የትምህርት አመራሩ ጋር ተቀናጅቶ ይሰራል፡፡ ከገለአሉ ወረዳ የፖሊስ ኢንስፔክተር መሃመድ አሊ ከዚህ በፊት በብሄራዊ ፈተና ሂደት ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮች የትምህርት አመራሩ ስራ ብቻ የጽጥታ አካሉንም የሚመለከቱ በመሆናቸው ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡ የኮሬ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ባለሙያ አቶ አብዱ ሃሰን በበኩላቸው ጥገኛ አመለካከት በማስወገድ ኃላፊነት ያለው ትዉልድ ለማፍራት የጋራ ርብርብ እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል፡፡ የትምህርት ተቋማት  በግል ችሎታና ብቃት ተወዳድሮ ማሸነፍ የሚችል፣ በስነምግባር የታነጸና ለህብረተሰብ ችግሮች መፍትሄ የሚያፈልቅ  ትውልድ ለመገንባት ለሁሉም ወገን ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል። በምክክር መድረኩ ላይ ከ32ቱም ወረዳዎች የተውጣጡ የትምህርትና የጸጥታ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም