የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን በተመለከተ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ለዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች ገለጻ ተደረገ

68

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11/2013 ( ኢዜአ) የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የ2013 የአረንጓዴ አሻራን በተመለከተ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች ገለጻ አደረጉ።

የሚኒስትሩ ገለጻም ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ግቦችና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ግንባታ ያላትን ቁርጠኝነትና አጠቃላይ የመርሃ ግብሩን ዓላማ ለማስገንዘብ መሆኑ ተገልጿል።

ከሶስት ዓመታት በፊት የተጀመረው የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ዘንድሮ "ኢትዮጵያን እናልብሳት" በሚል መርህ ይተገበራል።

የ"ኢትዮጵያን እናልብሳት"  መርሐ ግብርንም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በትናንትናው ዕለት በይፋ አስጀምረዋል።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 7 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል።

ከዚህ ውስጥ 1 ቢሊዮን ችግኞች ለጎረቤት ሀገራት የሚቀርብ ሲሆን ይህም ኢትዮጵያ አፍሪካን በጋራ የመልማት እቅድ ለማገዝ የድርሻዋን ለመወጣት ያለመ ነው።

በኢትዮጵያ ለሚገኙ ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች የተደረገው ገለፃ ዋነኛ ዓላማም በመርሃ ግብሩ ላይ የድርሻቸውን አስተዋፆ እንዲያደርጉ መሆኑ ታውቋል።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ25 ሚሊዮን በላይ ዜጎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም