ዳኝነቱን ለባለቤቱ

84

አብዱራህማን  ናስር (ኢዜአ)

የዴሞክራሲያዊ  አስተዳደር  ሥርዓት  በሚከተሉ  ሀገራት  ዜጎች ሀሳባቸውን  በነፃነት  የሚገልጹበት  እና የሚያስተዳድሯቸውን አካል ወደ ሥልጣን እንዲመጣ የሚያደርጉበት አንዱ መንገድ ምርጫ ነው።

 ምርጫ የአንድ ሀገር የዴሞክራሲያዊ አስተዳደር  ጽንሰ  ሀሳብ  እየዳበረ  የሚሄድበት ፣ የዜጎች  የስልጣን  ባለቤትነት የሚረጋገጥበትም  ሂደት ነው።

 ዜጎች በምርጫ አማካኝነት የመንግስት አስተዳደር በየደረጃው ያቋቁማሉ፣ በዚህም  የ`ሃላፊነትና  የተጠያቂነት ሥርዓት እንዲሰፍን ያደርጋሉ።

በኢፌዴሪ  ሕገ  መንግስት  መሰረታዊ  መርሆዎች በሚል  ከተገለጹት መካከል አንዱ የህዝብ ሉአላዊነት ነው።  በህገ መንግስቱ አንቀጽ 8 ላይ “የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው።

ሉአላዊነታቸውም  የሚገለጸው በዚህ  ህገ መንግስት መሰረት በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት  ዴሞክራሲያዊ  ተሳትፎ  አማካይነት  ይሆናል”  በማለት ይደነግጋል።  በዚህም  መሰረት በየአምስት ዓመቱ ህዝቡ ይበጀኛል፣ ያስተዳድረኛል የሚለውን አካል ከቀረቡለት አማራጮች መካከል  ይመርጣል።

 የስልጣን ባለቤት ህዝብ እንደመሆኑ መጠን የምርጫውን ሂደት በተመለከተ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና ተአማኒነት ያለው ስለመሆን አለመሆኑ ማረጋገጫ    ይሰጣል ማለት ነው።

ዘንድሮ በግንቦት ወር መጨረሻ ላይ ለ6ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።

የዘንድሮው የሀገራችን ምርጫ ለኢትዮጵያውያን የተለየ ዕድል የሚፈጥር ስለመሆኑ ብዙዎች ይናገራሉ።

ይህ ምርጫ በሀገሪቱ ከሶስት ዓመት በፊት ከተካሄደው ለውጥ ወዲህ የሚከናወን የመጀመሪያ ምርጫ በመሆኑ በተሳካ መልኩ ማከናወን ከተቻለ ለዴሞክራሲያዊ ሽግግር መሰረት የሚጥል ስለመሆኑም በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ እየተነገረ ይገኛል።

በተለይ ቀደም ሲል የተአማኒነት ችግር ሲነሳበት የነበረው የምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ሆኖ መደራጀቱ የምርጫውን ዴሞክራሲያዊ ሂደት እንዲጠናከር በማድረግ በኩል ጉልህ ሚና እንደሚኖረው የተለያዩ አስተያየት ሰጪዎች ሲናገሩ ይደመጣል።

በሌላ በኩል ከውስጥም ከውጭም የተለያዩ ተዋናዮች የምርጫውን ሂደት ለማደናቀፍ ዘመቻ ከፍተዋል።

እነዚህ ተዋናዮች ምርጫው የሚካሄድበት ወቅት እየተቃረበ ሲመጣ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የጸጥታ ችግር እንዲፈጠርና ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ለጥቃት በማጋለጥ ስጋት እንዲፈጠርባቸው በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛል።

 ይህንንም የጸጥታ ችግር እንደመነሻ በመውሰድ “በዚህ ወቅት ምርጫ ማድረግ ቅንጦት ነው” ሲሉ  ይደመጣሉ።

የውጭ ሃይሎች ደግሞ ከወዲሁ ምርጫው ነፃ፣ ፍትሃዊና ተአማኒነት የለውም ሲሉ መፈረጅ ጀምረዋል።

በቅርቡ አምስት የአሜሪካ ሴናተሮች ኢትዮጵያ በግንቦት ወር የምታካሂደው ምርጫ አሁን ባለበት ሁኔታ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን አያሟላም ሲሉ መግለጫ አውጥተዋል።

ሴናተሮቹ ቤንጃሚን ኤል ካርዲን፣ ቲም ኬይን፣ ጃኪ ሮስን፣ ኮርይ ኤ ቡከር እና ኤድዋርድ ጄ ማርኬይ ሲሆኑ ይህን ያቀረቡት ለአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስተዳደር የአፍሪካ  ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጆፍሪ ፌልትማን በጻፉት ደብዳቤ ነው። በደብዳቤው ላይ ከተጠቀሱት መካከል “የታቀደው ምርጫ የዓለምአቀፍ ስታንዳርድ ደረጃዎችን የሚያሟላ አይደለም፡፡

....በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከምርጫው ለመውጣት እያቀዱ ነው፡፡ መንግስት በሺዎች የሚቆጠሩ የተቃዋሚ መሪዎችን እያሰረ ነው። መንግስት ምርጫው አመኔታን ለማትረፍ ከፈለገ ከምርጫው በፊት ሁሉንም ያሳተፈ ውይይት (National Dialogue) ማድረግ አለበት። ይህ ሳይደረግ አሁን ባለበት ሁኔታ ከቀጠለ በመላ ሀገሪቱ እየጨመረ ያለው  የጎሳና  የፖለቲካ  ውጥረት ወደ ከፍተኛ ብጥብጥ ይቀየራል የሚል ስጋት አለን፡፡”  የሚለው  ዋነኛው  ነው።

በመሰረቱ የአሜሪካ ሴ ናተሮች  ደብዳቤ የሚያመለክተው የአንድን ሉአላዊ ሀገር ዜጎች የስልጣን ባለቤትነት በመንጠቅ ፈላጭ ቆራጭ መሆንን ነው።

 ምርጫው ነፃ፣ ፍትሀዊና ዴሞክራሲያዊ መሆኑን የማረጋገጥ መብቱ የስልጣኑ ባለቤት የሆነው  የኢትዮጵያ ህዝብ እንጂ የሌላ አካል ሊሆን አይችልም። የአፍሪካ ጉዳዮች የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተንታኝ ሎረንስ ፍሪማን ሴናተሮቹ የጻፉትን ደብዳቤ እጅግ አደገኛ መሆኑን “US Senators’ Call for Postponing Ethiopian Elaection is Foolish and Very dangerous” በሚል ርእስ በፃፉት ትንታኔ ላይ ተችተዋል።

የፖለቲካል ኢኮኖሚ ምሁሩ ሎረንስ ፍሪማን በትንታያቸው ሴናተሮቹ በደብዳቤያቸው ላይ በኢትዮጵያ ግጭት እንዲፋፋም ፍላጎት እንዳላቸው እንደሚያሳይ በመጠቆም ሀገራዊ ምርጫ መካሄድ የለበትም በማለት ያቀረቡት ሃሳብ እጅግ አደገኛ ነው በማለት አብራርተዋል፡፡

ከዚሁ በተጨማሪ አንዲት ሉዓላዊት ሀገር ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት በምታደርግበት ወቅት ድጋፍ ማድረግ ሲገባ የምእራባውያን እብሪተኝነት ግን እንዲህ ሃላፊነት የጎደለው ነው ብለዋል። ሴናተሮቹ ጭራሽ ስለኢትዮጵያ ህዝብ ማንነት ፍፁም እውቀት የላቸውም በማለት የገለጹት ተንታኙ ከ125 ዓመት የአድዋ የድል ታሪክ ጀምሮ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ የህዝቡን አንድነት ለማጠናከር የጀመሩትን ሂደት ግንዛቤ የላቸውም ሲሉ ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአሜሪካ ሴናተሮቹ የጠቀሷቸው ጉዳዮች በተመለከተ በሰጠው ምላሽ ቦርዱ ገለልተኛ ተቋም እንደመሆኑ ቀጣዩ ምርጫ ዓለም አቀፍ ሕግጋት የተከተለ እንዲሆን ጥረት እያደረገ መሆኑን አመልክቷል።

በአሁኑ ወቅት በቦርዱ ከተመዘገቡ 49 የፖለቲካ ፓርቲዎች 46ቱ ዕጩዎቻቸውን ማሳወቃቸውንም ገልጿል።

 በፌዴራልና በክልል ደረጃ 9 ሺህ ዕጩዎች እንደሚሳተፉ የጠቆመው የቦርዱ መግለጫ ይህም በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ እስከዛሬ ከተመዘገበው ትልቁ መሆኑን ተጠቅሷል።

ከዚህ በተጨማሪ ከ190 በላይ ሃገር በቀል የሲቪክ ማህበራት ግንዛቤ እንዲያስጨብጡ ፈቃድ እንደተሰጣቸው፣ 34 ሃገር በቀል ድርጅቶች ደግሞ ምርጫውን እንዲታዘቡ ፈቃድ ማግኘታቸውን ተገልጿል።

 የፖለቲካ ፓርቲዎችና ዕጩዎች በምርጫ ሂደቱ ላይ በሃገሪቱ የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ እንደሆነም በመግለጫው ተመልክቷል።

የምርጫውን ሂደት ከወዲሁ ብይን የመስጠት አባዜው የአውሮፓ ህብረትንም ይመለከታል። ህብረቱ በተደጋጋሚ

ሲያወጣቸው በነበሩ መግለጫዎች በኢትዮጵያ ከምርጫው በፊት ሁሉን አሳታፊ ድርድር መካሄድ እንዳለበት ሲያሳስብ ቆይቷል።

ከምርጫው በፊት ድርድር ካልተደረገና በኢትዮጵያ ያለው ግጭት ካልቀነሰ የምርጫ ታዛቢ ቡድን እንደማይልክ

ሲያስፈራራ ሰንብቷል። በቅርቡ በሰጠው መግለጫ “ሁኔታዎች ባለመሟላታቸው የምርጫ ታዛቢ ልዑክ የመላክ ዕቅዱ ተሰርዟል” ማለቱ  ይታወሳል።

 የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ይህንን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ “እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎችን ማቅረባቸው በተዘዋዋሪ እኔ ላስተዳድራችሁ እንደማለት ነው” ሲሉ ነው የገለጹት። ህብረቱ ተጸጽቶ ይሁን ባይታወቅም በኋላ ላይ ደግሞ ምርጫውን የሚታዘቡ ኤክስፐርቶች እልካለሁ ማለቱን አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።

የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች መምጣት አለመምጣት በተመለከተ በአገራዊው የምርጫ ሂደት ረጅም ጊዜ

ተሳትፎ በማድረግ የሚታወቁት የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ሲገልጹ “ታዛቢዎቹ ባለፉት ምርጫዎች ወቅት ውዝግብን ከመጫር ባሻገር የፈየዱልን አንዳችም ነገር የለም” ሲሉ ገልጸዋል።

 ፕሮፌሰር በየነ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳስታወሱት በተለይ በ1997 ሀገር አቀፍ ምርጫ ወቅት የአውሮፓ ህብረት ያወጣው መረጃ እንደ ሀገር ብዙ ትርምስ የፈጠረና ዋጋ የተከፈለበት ነበር።

ከዚህ አንጻር አሁን ላይ አንመጣም ማለታቸው የሚያጎለው አንዳችም ነገር የለም፤ እኛም አንጠብቃቸውም ሲሉ አክለዋል።

የውጭ ታዛቢዎች መቅረታቸው እንደውም የውስጥ አቅማችንን ተጠቅመን ምርጫውን ተዓማኒ እንድናደርገው እድል የሚሰጥ ይመስለኛል በማለት ነበር የገለጹት።

ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት የምታካሂደው ሀገር አቀፍ ምርጫ ከህዳሴው ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ጋር ተዳምሮ የውጭ ሃይሎች ጫና እጅግ እየበረታ የመጣበት ሁኔታ እየተስተዋለ ነው።

ኢትዮጵያን ለማዳከም ከውስጥና ከውጪ በመቀናጀት ሁለቱን ትላልቅ ሀገራዊ አጀንዳዎች ለማደናቀፍ ከምንጊዜውም በላይ በመረባረብ ላይ ናቸው።

 ከአሜሪካ እስከ አውሮፓ ብሎም ግብጽ እና ሱዳን ምርጫው እንዳይካሄድና የህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት እንዲስተጓጎል በጀት መድበው ከፍተኛ ሩጫ በማድረግ ላይ ናቸው። አሁን በየቦታው የሚታየው የዜጎች ግድያና መፈናቀል የዚሁ ተልዕኮ አካል ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም።

የአሜሪካና የአውሮፓ ህብረት ዋነኛ ዓላማ ሁሉን ነገር በእነርሱ መለኪያ እንዲለካና በሚፈልጉት መንገድ እንዲካሄድ ግፊት ማድረግ ነው። ይህንንም ለማሳካት በተናጠልም ይሁን በጋራ ማስጠንቀቂያ አዘል መግለጫዎችን እያወጡ ነው፤ በቀጣይም ሂደቱ እነርሱ በሚፈልጉት መንገድ እንዲሄድላቸው ምርጫው እሰከሚጠናቀቅ ድረስ ይህ ተጽእኖ ምናልባትም ቢጨምር እንጂ ይቀንሳል ተብሎ አይገመትም።

በምርጫው ማንም ያሸንፍ ማን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት መካሄዱ በራሱ አሁን ያለውን ሁኔታ ሙሉ በመሉ እንደሚቀይረው ይታመናል። ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ መሪዎቹን ለመምረጥ ካርድ ከመውሰድ ጀምሮ ለምርጫው አስፈላጊ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅበታል።

ይህ ምርጫ ከዴሞክራሲ ስርዓት መሰረት መጣል ያለፈ የሀገር ህልውናን የሚያስቀጥል ታሪካዊ ምእራፍ ነው። ህዝቡ የሀገሪቱ የሉአላዊ ስልጣን ባለቤት ነውና በምርጫው ንቁ ተሳታፊ በመሆን በእጁ ያለውን መብት ሙሉ በሙሉ መጠቀም አለበት።

ምርጫው ነፃ፣ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተአማኒነት ያለው ስለመሆኑ ዳኝነት የሚሰጠውም ራሱ ህዝቡ እንጂ ሌላ ወገን አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም