በጋምቤላ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው

72
ጋምቤላ ግንቦት 7/2010 የሴቶችን አቅም በማጎልበት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን የጋምቤላ ክልል ሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ፡፡ የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ አጁሉ ኡቻር ለኢዜአ እንደገለጹት ቢሮው ሴቶችን በተለያዩ የክህሎት ስልጠናዎች አቅማቸውን በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እየሰራ ነው። በክልሉ ትምህርታቸውን አጠናቀው ሥራ አጥ የሆኑ ወጣት ሴቶችን ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ በኮምፒዩተር ሳይንስ፣ በግብርናና በሌሎችም የሙያ መስኮች መሰረታዊ የሥራ ክህሎት ሥልጠና እንደተሰጣቸው ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ወጣት ሴቶች የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ ለማመቻቸት ቢሮው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለእዚህም ከአውሮፓ ሕብረት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ቢሮው ከሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለ500 ወጣት ሴቶች የሙያና የክህሎት ሥልጠና በመስጠት ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተደረገ ያለውን ጥረት በማሳያነት ጠቅሰዋል ። በክልሉ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክትም ጠይቀዋል፡፡ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ግሩም ገብረኢየሱስ በበኩላቸው ወጣቶቹን በግብርና፣ በእንስሳት እርባታና ማድለብ፣ በዶሮ እርባታ፣ በማር ማቀነባበር የሥራ ዘርፎች ለማሰማራት ለሁለት ወራት የተግባርና የክህሎት ሥልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡ ወጣቶቹ ከስልጠና በኋላ ቀጥታ ወደ ሥራ እንዲገቡ በተዘዋዋሪ የገንዘብ ብድርከ ከ17 ሺህ እስከ 20 ሺህ ብር ተጠቃሚ ይሆናሉ ። ፕሮጀክቱ በክልሉ ሦስት ወረዳዎች የሚገኙ ወጣቶችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም አስረድተዋል። በጋምቤላ ከተማ የቀበሌ 03 ነዋሪ ወጣት አጁሉ ፒተር በሰጠችው አስተያየት እየተሰጣት ባለው የእንስሳት እርባታና ማድለብ ሥልጠና የተሻለ ግንዛቤ ማግኘቷን ገልጿለች ፡፡ ባገኘችው እውቀትና ክህሎት በመጠቀም በከተማ የወተትና የስጋ ፍላጎት አቅርቦት ዘርፍ ለመሰማራት ማሰቧን አመላክታለች። " ቀደም ሲል ስልጠና በወሰድንበት ማር የማቀነባበር ሥራ ተሰማርተን ገቢያችን እያሳደግን ነው "  ያለችው ደግሞ በከተማው የቀበሌ 05 ነዋሪ ወጣት ባንቻየሁ ታፈሰ ናት፡፡ ፕሮጀክቱን በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች በማስፋፋት ከ7 ሺህ በላይ ወጣት ሥራ አጥ ሴቶችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም