ከአሰላ ወደ አዳማ ሲጓጓዝ የነበረ 39 ቦንዳ ልባሽ ጨርቅ ተያዘ

96
አዳማ ግንቦት 7/2010 ትናንት ከሌሉቱ 7፡00 ሰዓት አካባቢ ከአሰላ ወደ አዳማ ከተማ ልባሽ ጨርቆችን ይዞ ይጓዝ የነበረ አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ በቁጥጥር ስር መዋሉን የፌዴራል ፖሊስ አስታወ በፌዴራል ፖሊስ የፈጥኖ ደራሽ ዳይሬክቶሬት ምስራቅ ሪጅን 3ኛ ሻለቃ 4ኛ ሻምበል አዛዥ ኢንስፔክተር ተጫነ አረፈ እንደገለጹት፤ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-35383 (አ.አ) አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ ሊያዝ የቻለው 39 ቦንዳ ልባሽ ጨርቅ ጭኖ ከአሰላ ወደ አዳማ እያመራ ባለበት ወቅት ከህዝብ በደረሰ ጥቆማ ነው። ኢኒስፔክተር ተጫነ እንዳሉት ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ከአዳማ ከተማ ወጣ ብሎ ቢጠባበቅም የመኪናው አሽከርካሪ መረጃ ደርሶት አቅጣጫ ቀይሮ ሰዋራ ቦታ ላይ ተደብቆ ለመቆየት ሞክሮ ነበር፡፡ የፖሊስ አባላቱ ተሽከርካሪው ሲቀር ባደረጉት ፍለጋ መኪናው ቢገኝም ፍጥነቱን በመጨመርና ከኋላ የተገጠሙ ፓውዛ መብራቶችን አጉልቶ በማብራት ከፖሊስ ለማምለጥ ሞክሮ እንደነበር ተናግረዋል። የፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ አባላት ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት አዋሽ መልካሳ አካባቢ ተሽከርካሪው ሊያዝ ቢችልም ሾፌሩ ዘሎ ማምለጡን ነው ኢንስፔክተር የገለጹት። የጭነት ተሽከርካሪው ሰሌዳ በግልጽ በማይታይ ቦታ ከመቀመጡ በላይ ከኋላው ለእይታ አስቸጋሪ የሆኑ ፓውዛ መብራቶች መገጠማቸው  ሆን ተብሎ ለኮንትሮባንድ ስራ የተዘጋጀ ነው የሚል ጥርጣሬ ማሳደራቸውን ተናግረዋል። ተሽከርካሪው ጭኖት የነበረው 88 ሺህ 275 ብር የሚገመትና 3 ሺህ 531 ኪሎ ግራም የሚመዝን 39 ቦንዳ ልባሽ ጨርቅ ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዛሬ ረፋዱ ላይ ገቢ ተደርጓል።   የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ አገርን የሚጎዳ ህገወጥ ተግባር በመሆኑ ሕብረተሰቡ ለፖሊስ ጥቆማ በማድረግ የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል ኢንስፔክተር ተጫነ መልዕክት አስተላልፈዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም