የመኪና ማቆሚያ እጥረትን ለመፍታትና የትራፊክ ፍሰቱን ለማሻሻል እየሰራሁ ነው -- የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ

88

ግንቦት 4/2013 (ኢዜአ) የመዲናዋን የመኪና ማቆሚያ ችግር ለመፍታትና የትራፊክ ፍሰቱንም በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ እየሰራሁ ነው ሲል የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ገለፀ።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ጅሬኛ ሂርጳ ለኢዜአ እንደተናገሩት በከተማዋ የሚስተዋለውን የፓርኪንግ ችግር ለመፍታት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጋራ እየተሰራ ነው።

የከተማዋን የትራፊክ ፍሰት ለማሻሻል በተያዘው ዓመት አራት አደባባዮች ፈርሰው በትራፊክ ማስተላለፊያ መብራት እንዲተኩ በመደረጉ በአካባቢዎቹ የትራፊክ መጨናነቅ ችግርን መፍታት ተችሏል ብለዋል።

በቅርቡም የዳያስፖራ አደባባይ ወደ ትራፊክ ማስተላለፊ መብራት እንደሚቀየር ጠቁመዋል።

የመንገድ ደህንነት ግንዛቤን ለማሳደግ በ10 ቦታዎች ተለዋዋጭ ምስል ለአሽከርካሪዎችና ለእግረኞች የሚያስተላልፉ 'ቫርየብል ሜሴጅ' የተሰኙ ሳይቦርዶች መተከላቸውንም አክለዋል።

በከተማዋ በ80 የተለያዩ ቦታዎች የትራፊክ ማስተላለፊ መብራቶች መተከላቸውንና በተያዘው ዓመትም የትራፊክ ምልክቶችና የቀለም ቅብ ሥራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።

ኤጀንሲው የትራፊክ ማኔጅመንት ስርዓቱን በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ እየሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት።

ዘመናዊ የእግረኛ ማስተላለፊያ የትራፊክ መብራት ባለፈው ዓመት ከቦሌ እስከ መስቀል አደባባይ፤ ዘንድሮም በቀላል ባቡር መንገድ ላይ መተግበር መጀመሩንም አቶ ጅሬኛ ተናግረዋል።

ለአውቶቡስ የተለዩ መስመሮች ላይ ቁጥጥር እየተደረገ በመሆኑ የአውቶቡሶችን ፍጥነት በመጨመር የመመላለስ አቅማቸውን እስከ 50 በመቶ ማሳደግ እንደተቻለም ጨምረው ገልፀዋል።

ለዚህ አብነት ሲጠቅሱም ከጀሞ ሜክሲኮ በአንድ ጉዞ ይወስድ የነበረውን ደቂቃ ከ50 ወደ 15 ማውረድ ተችሏል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም