ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ

162
አዲስ አበባ ሀምሌ25/2010 በውጭ አገር የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ኢትዮ-ዲያስፖራ ኮሙዩኒኬሽን አስታወቀ። በኢትዮ ዲያስፖራ ሬዲዮ መስራች ጋዜጠኛ ኢሳያስ ልሳኑ የተጻፉ በሰብአዊ ዕርዳታ እና በሥነ ምግባር ትውልድ መገንባት ላይ ያተኮሩ ሁለት መጽሐፍት በትናንትናው ዕለት በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተመርቋል። የኢትዮ-ዲያስፖራ ኮሙዩኒኬሽን ተወካይ ወይዘሮ ቅድስት አቤነዘር እንደገለጹት በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕክምና አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ችግሎችን ለማስወገድ በውጭ አገር የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያ ድጋፍ እንዲያደርጉ እንሰራለን ብለዋል። አብዛኛው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ወደ አገሩ ሲመለስ በተለያዩ የልማትና የማህበራዊ ሥራዎች ላይ ተሳትፎ ሲያደርግ የሚታይ መሆኑን የጠቆሙት ወይዘሮ ቅድስት በጤና አገልግሎትና በሰብአዊ ድጋፍ ሲሳተፍ አይታይም ብለዋል። በተለይ ለጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ድጋፍ ማድረግ ያስፈለገው በመላው አገሪቱ ከሚገኙ የጤና ተቋማት በሪፈራል የሚመጡ ሕሙማን የሚበዙበት ሆስፒታል በመሆኑ አስረድተዋል። የሆስፒታሉ የሥራ ኃላፊዎች በተደረገላቸው ማብራሪያ መሠረት ለበርካታ ሕሙማን የህክምና አገልግሎት የሚሰጥበት በመሆኑ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ የኀብረተሰብ ክፍሎችን ድጋፍ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል። ድጋፉን ስኬታማ ለማድረግም በውጭ አገር የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በሆስፒታሉ ያለውን ችግርና በሕክምና ባለሙያዎች በኩል ያሉ የሥነ ምግባርና የሰብአዊ ሥራዎችን ለማስተዋወቅ በሬዲዮ እና በቴሌቪዥን መገናኛ ብዙኃን መረጃዎችን እንደሚያሰራጩም አስረድተዋል። የኀብረተሰቡን የጤና ችግር ለመርዳትና የሕሙማንን ህይወት ለማትረፍ የሚሰጠውን አገልግሎት መደገፍ ትልቅ የሰብአዊነት መገለጫ በመሆኑ እኛ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በምናደርገው ድጋፍ መንፈሳዊ እርካታ የምናገኝበት ተግባር ነው ብለዋል። በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝ ሆስፒታል የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ክሊኒካል ሰርቪስ ዳይሬክተር ዶክተር ይርጉ ገብረሕይወት በበኩላቸው ሆስፒታሉ በዓመት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሕሙማን የሕክምና አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል። በሆስፒታሉ የሕክምና አገልግሎት ከሚያገኙ ህሙማን ውስጥ 67 በመቶ የሚሆኑት የድሃ ድሃ የኀብረተሰብ ክፍል እንደሆኑ የጠቆሙት ዶክተር ይርጉ ለ210 ሺህ ህሙማን ነፃ የህክምና አገልግሎት ያገኙ ሲሆን አገልግሎቱ በብር ሲተመን ከ89 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆነም ገልጸዋል። በሆስፒታሉ ሰራተኞች የተመሠረተው ጎጆ የበጎ አድራጎት ድርጅት የድሃ ድሃ የሆኑ ተመላላሽ ሕሙማን ለመድኃኒት መግዣ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ ከማድረጉም በተጨማሪ ከተለያዩ አገሪቱ አካባቢዎች ለሚመጡ ታካሚዎች የምግብ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል። እንደ ዶክተር ይርጉ ገለጻ በሆስፒታሉ ከሚገኙ የሕሙማን አልጋዎች በተጨማሪ የድሃ ድሃ የሆኑ ተመላላሽ ታካሚዎች የሚተኙበት 60 አልጋዎች በድርጅቱ በኩል ያገኛሉ። ለበጎ አድራጎት ድርጅቱ ከሆስፒታሉ ሰራተኞች በዓመቱ ከ15 እስከ 20 ሺህ ብር ገቢ የሚደረግ ሲሆን በኢትዮ ዲያስፖራ ኮሙዩኒኬሽን በኩል 10 ሺህ ብር ድጋፍ ተደርጎለታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም