የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ያስገነባውን ቤተ ሙከራ አስመረቀ

933

አዲስ አበባ ግንቦት 3/2013 (ኢዜአ) የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ከስቴም ፓወር ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ያስገነባውን ቤተ ሙከራ አስመረቀ።

የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ከስቴም ፓወር ባገኘው ድጋፍ ያስገነባውን ቤተ ሙከራ በዛሬው እለት በቃሊቲ ከፍተኛ ማረሚያ ቤት አባ ሳሙኤል ግቢ የታራሚዎች ትምህርት ቤት ውስጥ አስመርቋል።

በዚህ ወቅት ኮሚሽኑ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሚላኩ የህግ ታራሚዎችን በማስተማርና በማሰልጠን የእውቀት እና የሙያ ባለቤት እያደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ቤተሙከራው ታራሚዎች በቀለም ትምህርት በንድፈ ሀሳብ የተማሩትን በተግባር እንዲለማመዱ የሚያግዝ መሆኑም ተጠቁሟል።

ቤተሙከራውስቴም ፓወር ከተሰኘ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅት በተገኘ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ እንደተገነባም በምረቃው ላይ ተገልጿል።

የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል ዳመነ ዳሮታ እንዳሉት ኮሚሽኑ ታራሚዎች ከዚህ ሲወጡ በቀጣይ ለሚኖራቸው ህይወት ጠቃሚ የሆኑ ስልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል።

ስቴም ፓወር በተገኘው ድጋፍ ዛሬ የተመረቀው ቤተ ሙከራም የዚሁ አካል መሆኑን ነው ያመለከቱት።

እንደእርሳቸው ገለጻ ቤተሙከራው ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው በተግባር ልምምድ በመታገዝ ብቁና ተወዳዳሪ ሙያተኛ ሆነው እንዲወጡ ለማስቻል ያግዛል።

የስቴም ፓወር ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ቅድስት ገብረአምላክ በበኩላቸው ድርጅቱ ባለፉት 13 ዓመታት 48 የቤተ-ሙከራ ማዕከላትን መገንባቱን ገልጸዋል።

በቀጣይም 11 ማዕከላትን ለመገንባት ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

ታራሚዎች ከቦታ ቦታ ስለማይንቀሳቀሱ የተመረቀው ቤተ-ሙከራ ታራሚዎች ባሉበት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ከእስር ሲፈቱ በተግባር የተደገፈ እውቀት ይዘው ከማህበረሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ ለማድረግ ጭምር መሆኑን አስረድተዋል።

አስተያየታቸውን የሰጡ ታራሚዎችም ቤተ ሙከራው እስካሁን በንድፈ ሀሳብ የተማሩትን በተግባር ለማየት እድል እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል።

የማረሚያ ቆይታቸውን አጠናቀው ወደህብረተሰቡ ሲቀላቀሉ በተማሩት ትምህርት ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውንም ነው የገለጹት።