ለውጡን ለማስቀጠል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ የምክር ቤቱ አባላት ገለጹ

56
አሶሳ ሀምሌ25/2010 በኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡ የክልሉ ምክር ቤት ሰባተኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ ተጀምሯል፡፡ የምክር ቤቱ አባላት በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከተሾሙ ወዲህ የታየው ለውጥ የሀገሪቱን ህዝቦች ወደ አንድነት የሚያመጣና ሰላምን የሚያጠናክር ነው፡፡ ከአባላቱ መካከል አቶ ጌታነህ ሰዲ  በሰጡት አስተያየት " በምንኖርት ክፍለ ዘመን ብቸኛው አማራጭ ሠላም እና ተከባብሮ መኖር ነው" ብለዋል፡፡ እንደ ሀገር የተሻለ ለውጥ በሁሉም መስክ እንደሚያስፈልግ ገልጸው የክልሉ ህዝብና መንግስትም ፍላጎት ይኸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ሌላው የምክር ቤቱ  ወይዘሮ ፍሬህይወት አበበ በበኩላቸው እንደ ህዝብ ተወካይነታቸው የፌደራል መንግስት የህዝብ ፍላጎት መሠረት አድርጎ የጀመረውንና በሁሉም ህዝብ ተቀባይነት ያገኘውን ለውጥ ለማስቀጠል  አቅማቸው በፈቀደ እንደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡ አስፈጻሚውን አካል በመቆጣጠር በህዝብ የተጣለባቸውን ግዴታ እንደሚወጡ የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ሱአድ ሙሳ የተባሉት አባል ናቸው፡፡ አቶ ጌታነህ ሰዲ መግቢያ ለውጥ ሁልጊዜ እንቅፋት ሊገጥመው እንደሚችል ጠቁመው "ጥቅማቸው የተነካባቸው ጥቂት ግለሰቦች በቅርቡ በአሶሳ ከተማ የፈጠሩት የጸጥታ ችግር ለዚህ ማሳያ ነው "ብለዋል፡፡ የህዝቡ የልማትና መልካም አስተዳደር ፍላጎት በተሳሳተ አቅጣጫ ለማስኬድ የሚደረጉ ጥረቶችን ለማስቆም እንደሚሰሩም አባላቱ አመልክተው የውጡን ሂደት አጠናክሮ  ለማስቀጠል  አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ በአሶሳ ከተማ ዛሬ በተጀመረው  ጉባኤ የክልሉን የ2010 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም  ሪፖርት በርዕሰ መስተዳድሩ  ቀርቦ ውይይት ተካሄዶበታል፡፡ ጉባኤው እስከ ሐምሌ 27/2010ዓ.ም. በሚያደርገው ቆይታም  የክልሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ሪፖርቶች እንደሚቀርቡ እንዲሁም አራት ረቂቅ አዋጆች እንደሚጸድቁም ይጠበቃል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም