የደረሱ የበልግ ሰብሎችን እየሰበሰቡ መሆናቸውን የጊኒር ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ

103
ጎባ ሀምሌ25/11/2010 የምርት ብክነትን ለመከላከል የደረሱ የበልግ ወቅት ሰብሎችን በኮምባይነር እየሰበሰቡ መሆናቸውን በባሌ ዞን አስተያየታቸውን የሰጡ የጊኒር ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ። የዞኑ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት በበኩሉ እስካሁን 50 ሺህ ሄክታር ላይ የነበረ የደረሰ የበልግ ሰብል ከብክነት በፀዳ መልኩ መሰብሰቡን አስታውቋል። በወረዳው የሀረዋ ቀበሌ ነዋሪ አብዱልቃድር ሀሰን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በበልግ ወቅት ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ተጠቅመው በ1 ሄክታር ማሳ ላይ የዘሩትን የደረሰ የስንዴ ሰብል በኮምባይነር በመታገዝ ሰብስበዋል ። "ከሰበሰብኩት ሰብል 65 ኩንታል ምርት አግቺያለሁ" ሲሉም ተናግረዋል ። አርሶ አደር ሙስጠፋ አህመድ በበኩላቸው “በዘንድሮ የበልግ ወቅት በተለይ የጤፍ ሰብልን ከማሳ ላይ የሚሰበስብ ኮምባይነር ማግኘታችን በአጨዳ ወቅት ይደርስብን የነበረውን ድካም ከመቀነሱ በላይ የምርት ብክነትን አስቀርቶልናል” ብለዋል፡፡ "የአካባቢው አርሶ አደሮች በቡድን ተደራጅተን በኩታ ገጠም ማሳ ላይ የዘራነውን የደረሰ የስንዴ ሰብል በኮምባይነር ለመሰብሰብ ተራ እየጠበቅን ነው" ያሉት ደግሞ አርሶ አደር መሀመድ በከር ናቸው። የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ አለምእሸት አለማየሁ በዞኑ በበልግ ወቅት ታርሶ በዋና ዋና ሰብሎች በዘር የተሸፈነው ከ289ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ ነው። እስካሁንም በ50 ሺህ ኬክታር ላይ የነበረ የደረሰ ሰብል ከብክነት በፀዳ መልኩ መሰብሰቡን ነው የገለጹት። "የሰብል ስብሰባው በሰው ጉልበትና በኮምባይነር ታግዞ እየተካሄደ መሆኑን ገልፀው በቡድን የተደራጁ 120 ሺህ አርሶ አደሮችና ከ30 በላይ ኮምባይነሮች በሰብል ስብሰባ ሥራው ላይ መሰማራታቸውን ተናግረዋል ። በሰብል ስብሰባው በመሳተፍ ላይ ካሉ አርሶ አደሮች ውስጥ 10 ሺህ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውንም ጠቁመዋል። እንደ ባለሙያው ገለጻ አሁን በአካባቢው ባለ ዝናብ የደረሱ ሰብሎች ለጉዳት እንዳይዳረጉ አርሶ አደሩ በግብርና ባለሙያዎች ምክር ታግዞ ሰብልን ከማሳ ላይ በፍጥነት የመሰብሰቡን ሥራ አጠናክሮ ቀጥሏል። በባሌ ዞን ከሚያዝያ እስከ ሰኔ የበልግ ወቅት እርሻ የሚካሄድበት ሲሆን በዘንድሮ ዓመት በልግ ወቅት በስንዴ፣ ገብስ፣ ጤፍና በሌሎች ዋና ዋና ሰብሎች በዘር ከተሸፈነው 289ሺህ 200 ሄክታር መሬት ከሰባት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም