በጎነትና ነፃነት በእስልምና

149

በጎነትና ነፃነት በእስልምና

በሰለሞን ተሰራ 

ኢዜአ

ነፃነት 20ኛው ክፍለ ዘመን የወለደው ወይም ዘመናዊ አስተሳሰብ የፈጠረው ሳይሆን መለኮታዊና ለሰው ልጅ በነፃነት የተሰጠ ዓለም አቀፋዊ የሆነ ሃሣብ ነው። የሰው ልጅ ለራሱም ሆነ ለሌላው ማህበረሰብ ነፃነትን አይፈልግም ብሎ ማሠብም ስህተት ነው። 

አሁን ላይ በምዕራቡም ሆነ በምሥራቁ የዓለማችን ክፍል የሚኖሩ አንዳንድ አገራት ነፃነትን ለራሣቸው እንጂ ለሌሎች አሳልፈው መስጠት አይፈልጉም።

ይህንኑ ለማስተግበር የሚከተሉት ርዕዮተ ዓለም ትልቅ አፈናና ጭቆና በማስከተል የህዝቦችን ህይወት ፈታኝ ከማድረግ ባለፈ ለአገራት አለመረጋጋት ምክንያት ሆኗል።

የተለያዩ እምነቶች ሰላምንና ነጻነትን በመስበክ የሰው ልጅ ቀና ልቦና እንዲኖረውና እርስ በእርሱ እንዲረዳዳ መለኮታዊ መልዕክት በማስተላለፍ ያስተምራሉ፡፡

እስልምናም የሰው ልጅ በነፃነት እንዲኖር፤ ያለ አንዳች ፍራቻ በእኩልነት እንዲያስብና እንዲመኝ ሌሎችም ነፃነት ያገኙ ዘንድ እንዲሰራ ያስተምራል።

በቅዱስ ቁርዓን የነፃነት ፅንሠ ሀሣብ በተለያዩ ሁኔታዎችና ቃላቶች ተገልጿል።

“ሁር” ወይንም “ተህሪር”- ነፃነት አሊያም ባሪያን ነፃ ማድረግ፣ “ነጃት”- የደህንነት ዋስትና ማግኘት፣ “ፈውዝ”- የላቀ ስኬት በማስመዝገብ ከግብ መድረስ፣ “ፈላህ”- አስተማማኝ ደህንነት … የሚሉት ጥቂቶች ሲሆኑ በሀዲስ ደግሞ “ዒትቅ” የሚለው ቃል ነፃ ማውጣት /ነፃ ነህ/ ማለትን ያመለክታል።

ነፃነትና እኩልነት በጥብቅ የተሣሠሩ ነገሮች ናቸው። በእስልምና ደግሞ ለአላህ ባላቸው የፍራቻ ደረጃ ካልሆነ በስተቀር የሰው ልጆች ሁሉ እኩል ናቸው።

በመሆኑም ከነፃነት በፊት በእኩልነት ዙሪያ ብዙ መሥራት ከሰው ልጆችና ከእምነቱ ተከታዮች የሚጠበቅ ግዴታ መሆኑ ይነገራል።

እኩልነትን ሣንተገብር ነፃነትን መተግበር አይታሠብምና። በኢስላም ነፃነት ማለት የምንወዳቸውንና ስሜታችን የሚፈልጋቸውን ነገሮች ሁሉ አሣድዶ መተግበር (መሥራት) ሣይሆን በአላህ ዘንድ የሚወደዱ ጥሩ ነገሮችን መርጦ የመሥራት ነፃነት መሆኑን ማወቅ እንደሚገባ የእምነቱ አባቶች ያስተምራሉ፡፡

በዐረብኛ “ሁር”- ነፃ የሚለው ቃል ነፃነትን ብቻ ሣይሆም ክብርንም ያመለክታል። “የሰው ልጅ ነፃነት ይከበር” ሲባል ለሰብኣዊው ፍጡር ሁሉ ተገቢው ከበሬታ ይሠጠው ማለት ነው። 

በአጠቃላይ መልኩ እስልምና ነፃነትን ያበረታታል፣ ይደግፋል፣ ለነፃነትም ያነሳሳል። እስልምና ለሰው ልጅ መከበር ከፍተኛ ትኩረት የሚሠጥ የነፃነትና የክብር ሃይማኖት ነው። ሰዎች አእምሮአቸውንና መንፈሣቸውን ክፍት በማድረግም ካለሙት ግብ እንዲደርሱ ያግዛቸዋል። 

ነፃነት ትልቅ ክብር ነው። ከጭቆናና ውርደት ተላቆ ክብርን እስካላገኘ ድረስ የሰው ልጅ ነፃ ነው ማለት አይቻልምና።

የነፃነት ፅንስ ሀሣብ ዑቡዲያህ (አላህን መገዛት) ጋርም አይቃረንም። ኢስላም እራሱ ነፃነትን የሠጠን ሲሆን ፈጣሪያችንን አላህን መታዘዝና ማገልገል እንዳለብንም አስተምሮናል ይላሉ የእምነቱ አባቶች።

ነፃነት በኢስላም ከሞራላዊ ግዴታና ከተጠያቂነት አሊያም ከእውነተኝነት፣ ከፍትሃዊነት፣ ከበጎ ሠሪነትና ትክክለኛ ከመሆን ማፈንገጥ አይደለም። 

የኢስላም አስተምህሮ የሰው ልጆች ሁሉ በአእምሮ፣ በመንፈስም ሆነ በአካል ነፃ መሆን እንዳለባቸው ያዛል። ኢስላም ለሁሉም ህዝቦች የእምነት ነፃነትንም አረጋግጧል። በእምነትም ማስገደድ እንደሌለ አውጇል። ሱራህ አል በቀራህ (ሱረቱል በቀራህ) ቁጥር 256 ላይ የተመለከተውም ይሄው ነው። 

በመሆኑም ሰዎች ሁሉ እምነታቸውን በነፃነት ማራመድና የመተግበር መብት አላቸው ፣ ሆኖም ግን እምነታቸውን በግድ ሌሎች ላይ ለመጫን ሙከራ ማድረግ የለባቸውም።

እስልምና ለሰው ልጆች ሀሣብን በነፃነት የመግለፅ መብት ይሠጣል፤ ነገር ግን ሰዎች መሠረተ ቢስ ወሬዎችንና ውሸትን መናገር የለባቸውም።

ኢስላም ሰዎች በራሣቸው ፍላጎትና ስምምነት መሪዎቻቸውን እንዲመርጡና መሪዎቻቸውም ታማኝ ሣይሆኑ ሲቀሩ አሊያም ሀላፊነትን መወጣት ሲያቅታቸው ያወርዱ ዘንድ ነፃነትን ያስተምራል።

ኢስላም የኢኮኖሚ ነፃነትንም ይፈቅዳል፤ ሰዎች በነፃነት ሠርተው የማግኘትና የፈለጉትን ያህል የማከማቸት መብት ያላቸው ቢሆንም ያለ አንዳች ርህራሄ በማግበስበስ ለራሣቸው ብቻ የተንደላቀቀ ኑሮ በመኖር ለሌላው ባለማሠብና በማጭበርበር መሆን የለበትም የሚል ፅኑ አቋም አለው።

እስልምና የነፍስን፣ የእእምሮንና የአካል ነፃነትን ያስተምራል።

እስልምና የግለሰብንና የማህበረሰብ ነፃነትን ያስተምራል።

እስልምና በዚህኛውም ሆነ በመጭው ዓለም ነፃነትን ያስተምራል።

በሌላ በኩል ደግሞ ነፃነት አሉታዊና አዎንታዊ ገፅታዎች እንዳሉት መገንዘብ ይኖርብናል። ይሄውም አንድን ነገር ለመፈፀም ነፃነትን ማግኘትና ከአንድ ነገር ነፃ መውጣት ሊሆን ይችላል።

ኢስላም ነፃነትን የሚፈልገው ለደስተኛና ጤነኛ ህይወት እንዲሁም ለሞራላዊና ለተከበረ ህይወት ሲባል ነው።

ኢስላም የሰው ልጆች በነፃነት የአምልኮ ተግባራቸውን እንዲፈፅሙ፣ ሀሣባቸውን እንዲገልፁ፣ ሰርተው እንዲያገኙ፣ ቤተሰብ እንዲመሠርቱና ሌሎችንም መልካም ተግባሮች እንዲያከናውኑ ይመክራል።

ህዝቦች ሁሉ ከኢኮኖሚ፣ ከፖለቲካና ከማህበራዊ ጭቆና ፣ ከቁስ አምላኪነትና ከራስ ወዳድነት ነፃ እንዲወጡ ይፈልጋል። ሙስሊሞች ለራሣቸውም ሆነ በሌላው ዓለም በሚደረገው የነፃነት እንቅስቃሴ ግንባር ቀደም ተሣታፊ መሆንም ይኖርባቸዋል።

ስለ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና እምነት ነፃነት ከመናገር ወደ ኋላ ማለት አይገባቸውም።

ስለ ሰብአዊ መብት፣ በማህበረሰቡ ውስጥ አነስተኛ ቁጥር ስላላቸው ህዝቦች መብት፣ ስለ ሴቶች መብትም እንዲሁ ማንሣትና መታገል ይኖርባቸዋል በማለት ያስተምራል።

እነኚህ ሁሉ መብቶች በእስልምና ሙሉ እውቅናና ድጋፍ ተሠጥቷቸዋል። በመሆኑም የቁርኣንንና የሀዲስን መመሪያ እንዲሁም የቀደምት ሠለፎችን ፈለግ በመከተል ለመብቶችና ነፃነቶች በሙስሊሙ ማህበረሰብ ውስጥ ለማስረፅ በከፍተኛ ሁኔታ መጣር ይጠበቅብናል።

ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም ከመቆርቆር በመነጨ የሚቀርብ ምክንያታዊ ተቃውሞ በአላህ ዘንድ የሚጠላ ሊሆን አይችልም። እንዳውም የመሪዎችን ድክመትና የአመራር ክፍተት በመጠቆም (በተዘዋዋሪም ቢሆን) እነሱን ማገዝና መርዳት የሚቻልበት ዕድል አለ። 


ዓኢሻ (ረ.ዐ) እንዳስተላለፉት፣ የአላህ መልዕክተኛ (ሱ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል:-


"አላህ ለአንድ አስተዳዳሪ መልካም ሲሻለት፣ ሲረሳ የሚያስታውሰው፣ ሲያስታውስ የሚያግዘው፣ እውነተኛ ረዳት ይሰጠዋል። ከዚህ ሌላ ከሻበት ግን ቢረሳ የማያስታውሰው፣ ሲያስታውስም የማያግዘው ክፉ ረዳት ይሰጠዋል" ማለታቸውን ገልጸዋል። (አቡ ዳውድ ዘግበውታል)

ይሁንና መሪዎችን በሀሰት መወንጀልና መሠረተ-ቢስ አሉባልታ በመንዛት ከህዝብ ጋር ለማጋጨት መሞከር በአላህ ዘንድ የሚወደድ አይሆንም።


በተለይም በዚህ በተከበረው የረመዳን ወር ሀሰተኛ መረጃን ማሰራጨት አላህን ሊያስቀይምና ፆምንም ሊያበላሽ ይችላል። በተለይ ከፆም ጋር ተያይዞ፣ ከአቡ ሁረይራህ (ረ.ዐ) እንዘገቡት፣ የአላህ መልዕክተኛ (ሱ.ዐ. ወ) እንዲህ ብለዋል፦


"ሐሰተኛ ንግግርና በዚያው መሠረት መተግበርን የማይተው ሰው፣ ምግቡንና መጠጡን በመተው (ብቻ) ለአላህ ጉዳይ የለውም" (ቡኻሪ ዘግበውታል)


እዚህ ላይ ፈታኙ ጉዳይ ከሌሎች የምናገኛቸው (የምንሰማቸው) መረጃዎች ምን ያህል ትክክለኛ ናቸው? የሚለው ነው።


መቼም እዚህ በፌስቡክ መንደር የሚዘዋወረውንና በውስጥ መስመር (through inbox) የሚደርሰንን ሁሉ ተቀብለን እናስተጋባው ከተባለ እንደ ሀገርና እንደ ማህበረሰብ ገደል ሊከተን የሚችል ነው። ስለሆነም በተቻለ መጠን የመረጃውን ምንጭና ትክክለኛነት ለማረጋገጥ፣ ብሎም ምክንያታዊ ለመሆን መሞከር ተገቢ ነው።

አቡ ሁረይራ (ረ.ዐ) እንዳስተላለፉት፣ ነብዩ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል:- "ሰውዬው የሰማውን ሁሉ ማውራቱ ከውሸት በቂው ነው።" ስለሆነም በተቻለ መጠን የመረጃውን ምንጭና ትክክለኛነት ለማረጋገጥ፣ ብሎም ምክንያታዊ ለመሆን መሞከር ተገቢ ነው።


ከዚህ አንፃር፣ አቡ መሐመድ ሀሰን ኢብኑ ዐልይ ኢብኑ አቡ ጧሊብ (ረ.ዐ) እንዳስተላለፉት፣ የአላህ መልዕክተኛ (ሱ.ዐ.ወ) ጠቃሚ ምክር ሰጥተዋል።


"የሚያጠራጥርህን ነገር በመተው፣ የማያጠራጥርህን ያዝ። እውነት ውስጣዊ ሠላምና መረጋጋት ሲሆን፣ ሀሰት ደግሞ ጥርጣሬና የልቦና አለመረጋጋት ነው።" (ቲርሚዚይ ዘግበውታል)


ሀሰተኛ መረጃ የምናሰራጨውና ጭፍን ተቃውሞ የምናራምደው ለሥልጣን ካለን ጉጉት በመነጨ ከሆነ በአላህ ዘንድ የማይወደድና ፆማችንን ሊያበላሽ የሚችል ተግባር ነው ይላሉ።


አቡ ሁረይራ (ረ.ዐ) እንዳስተላለፉት፣ የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል:-


"እናንተ ለሹመት ትጓጓላችሁ፤ በመጭው ዓለምም ቁጭት ትሆንባችኋለች።" (ቡኻሪ ዘግበውታል)


በተመሳሳይ አቡ ዘር (ረ.ዐ) እንዳስተላለፉት፣ የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል "{ሥልጣን] በአግባቡ ካልያዙት እና [ኃላፊነቱን] ካልተወጡት በዕለተ ቂያማ ውርደትንና ቁጭትን ያስከትላል።" ማለታቸው ተዘግቧል።


ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች የተወሰደ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም