በአማራ ክልል ከ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ መራጮች ተመዝግበዋል

63

ባህር ዳር፣ ሚያዚያ 30 ቀን 2013 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ከ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ተመዝግቦ ለመምረጥ የሚያስችለውን ካርድ መውሰዱን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የአማራ ክልል ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እያንዳንዱ ፓርቲ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ለማስቻል የምክክር መድረክ ዛሬ በባህርዳር ከተማ ተካሂዷል።

የቦርዱ የአማራ ክልል ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መኳንንት መከተ እንደገለጹት፤ ፓርቲዎች በውድድር ሂደታቸው የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በሰለጠነ አግባብ በጋራ ውይይት መፍታት አለባቸው።

የጋራ ምክር ቤቱ ለምርጫው ዴሞክራሲያዊነትና ፍትሃዊነት የሚገባውን አስተዋጽኦ ሁሉ እያደረገ እንደሆነም ተናግረዋል።

አስር ሚሊዮን መራጭ ይመዘገባል ተብሎ በሚጠበቅበት የአማራ ክልል እስካሁን ከ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ መራጮች የምርጫ ካርድ መውሰድ መቻላቸውን አብራርተዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች አስፈጻሚዎች የሚያነሱትን የክፍያ ችግር ቦርዱ እየፈታ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለምዝገባ በተጨመረው የአንድ ሳምንት ጊዜ በስፋት የሚሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በክልሉ ካሉ 12 ሺህ 199 የምርጫ ጣቢዎች መካከል በ11 ሺህ 878ቱ የመራጮች ምዝገባ በተሟላ መልክ እየተከናወነ እንደሚገኝም ጠቅሰው፤ ቀሪዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች ሁኔታዎች ዝግጁ በሚሆኑበት ወቅት ስራ እንደሚጀምሩ አቶ መኳንንት አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም