የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩት የቻይና ሮኬት ያለበትን ሁኔታ እየተከታተለ ለህዝብ መረጃ እንደሚሰጥ ገለፀ

155

ሚያዚያ 30 ቀን 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩት የቻይና ሎንግ ማርች 5ቢ ሮኬት ያለበትን ሁኔታ እየተከታተለ መረጃ እንደሚሰጥ አስታወቀ።

የቻይና ሎንግ ማርች 5ቢ ሮኬት ከቁጥጥር ውጭ ከሆነበት ከሚያዝያ 21 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በከፍተኛ ፍጥነት በመሬት ዙሪያ እየተሽከረከረ ይገኛል።

በመሬት ዙሪያ አንዴ ለመዞር የሚፈጅበት ጊዜ 90 ደቂቃ ሲሆን ፍጥነቱም በሰዓት 28 ሺህ ኪሎ ሜትር ይደርሳል ተብሏል።

ሮኬቱ አሁን ባለበት ሁኔታ በመሬት ዙሪያ የመሽከርከር አቅሙን እያጣ በመምጣቱ ነገ ግንቦት 1 ቀን 2013 ዓ.ም ወደ መሬት ሊወድቅ እንደሚችል ይገመታል።

ሮኬቱ የት ሊወድቅ ይችላል የሚለውን በእርግጠኝነት መናገር እንዳይቻል ያደረገው ዋነኛ ምክንያት በመሬት ዙሪያ የሚጓዝበት ፍጥነት ከፍተኛነት ነው።

ይህ ማለት ወደ መሬት ከባቢ አየር ሊገባ የሚችልበትን ጊዜ ግምት ሊሰጥ የ30 ደቂቃ ያክል ልዩነት ቢኖር በሚያርፍበት ስፍራ ላይ የ10 ሺህ ኪሎ ሜትር ለውጥ ያመጣል ማለት ነው።

"ስለሆነም የሚያርፍበትን ቦታ ትክክለኛ ግምት መስጠት የሚቻለው ወደ መሬት ከባቢ አየር ክልል ገብቶ ወደ ታች መምዘግዘግ ከሚጀምርበት ጊዜ አንስቶ ይሆናል" ብሏል የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩት ለኢዜአ በላከው መግለጫ።

የቻይናን ሎንግ ማርች 5ቢ ሮኬት ምንነት፣ አሁን የሚገኝበትን ሁኔታና ሮኬቱ በአገራችን ቢወድቅ መወሰድ ስለሚገባቸው የጥንቃቄ እርምጃዎች በሚመለከትም ኢንስቲትዩቱ አብራርቷል።

ኢንስትቲዩቱ እንዳብራራው ስብርባሪው ኢትዮጵያ የማረፍ እድል አለው የለውም የሚለውን መናገር የሚቻለው ሮኬቱ መሽከርከሩን አቁሞ ወደ ከባቢ አየር መግባት እና ወደ መሬት መምዘግዘግ ከጀመረበት ቅፅበት አንስቶ ነው ብሏል።

ከዚህ ጊዜ አንስቶ ስብርባሪው ወደ መሬት ለመድረስ የሰዓታት ጊዜ ስለሚኖረው ቦታው እንደታወቀ የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባም ተመላክቷል።

ስብርባሪው የት እንደሚወድቅ ከታወቀ በእግርም ሆነ በተሽከርካሪ የሚደረግ እንቅስቃሴን መገደብ፣ ጠንካራ ከለላ ወይም የላይ ሽፋን ባለው ስፍራ ስር መሆን እንዲሁም ድንገት ስራ ላይ ከሆኑ ሔልሜት ማድረግ እና የመሳሰሉትን እርምጃዎች መውሰድ እንደሚገባ መግለጫው ያብራራል።

ሳተላይት ለማምጠቅ ጥቅም ላይ የሚውሉ ሮኬቶች ተልዕኳቸውን ከጨረሱ በኋላ ከቁጥጥር ሳይወጡ የመሬት ከባቢ አየር ክልልን አልፈው ተገማች በሆነ ስፍራ ወደ ውቅያኖስ እንዲገቡ ወይም ሰው በማይኖርበት ራቅ ያለ የመሬት አካል እንዲያርፉ ማድረግ የተለመደ አሰራር መሆኑ ተመላክቷል።

ለዚህ አገልግሎት በአብዛኛው የሚውለው በፓስፊክ ውቅያኖስ ደቡባዊ ንፍቀ ክበብ ከየብስ ርቆ የሚገኝ የውሃ አካል ነው።

5ቢ ሮኬት ከቁጥጥር ውጭ ስለሆነበት ምክንያት እስካሁን የተሰጠ የተሟላ ቴክኒካዊ ምክንያት ባይቀርብም ምናልባት ሮኬቱ ከሚጠበቀው በላይ ከፍታ እንዲወጣና ከተለመደው ፍጥነት በላይ እንዲጓዝ በመደረጉ ነው የሚሉ መላምቶች እየቀረቡ መሆኑም ተገልጿል።

ሮኬቱ ሙሉ በሙሉ መሬት ላይ እንደማይደርስ በእርግጠኝነት መናገር አይቻለም ያለው መግለጫው የምድር 71 በመቶ ውሃ በመሆኑ በየብስ ላይ የማረፍ እድሉ አነስተኛ ስለመሆኑም አብራርቷል።

ሮኬቱ ጉዳት የማድረስ እድሉ ያነሰ መሆኑን በመጠቆም ኢንስትቲዩቱ ሁኔታውን እየተከታተለ ለህዝቡ መረጃ እንደሚያደርስ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም