ኢትዮጵያ ከውስጥና ከውጭ የተጋረጠባትን ፈተና በጽናት ለማለፍ እያደረገች ላለው ጥረት የምሁራን ሚና ከፍተኛ ነው-ኤጀንሲው

79

ሆሳዕና፣ ሚያዚያ 30/2013( ኢዜአ ) ኢትዮጵያ ከውስጥና ከውጭ የተጋረጠባትን ፈተና በጽናት ለማለፍ እያደረገች ላለው ጥረት ስኬታማነት የምሁራን ሚና ከፍተኛ መሆኑን የኢፌድሪ ኢንፎርሜሽንና መረጃ መረብ ደህንነት ኤጀነሲ አስታወቀ።

ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛና በተከታታይ መርሀ ግብር በሆሳእናና ዱራሜ ካምፓሶች ያሰለጠናቸውን 1ሺህ 398 ተማሪዎች በአንደኛና ሁለተኛ ዲግሪ አስመርቋል ።

በተማሪዎች ምርቃት ስነ ስርዓት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት በኢፌድሪ ኢንፎርሜሽንና መረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንተነህ ተስፋዬ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ከውስጥና ከውጭ የተጋረጡባትን ፈተናዎች በጽናት ለማለፍ እያደረገች ባለው ጥረት የምሁራን ሚና ከፍተኛ ነው ።

ሀገሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በማልማት ተጠቃሚ እንዳትሆን ለማድረግ የውስጥና የውጪ ጠላቶች ከሚያሰራጩት የተዛባ ወሬ ምሁራን ራሳቸውን በማራቅ ባንጻሩ በጥናት የተረጋገጠ መረጃ በማቅረብ ትክክለኛውን እውነታ ማሳወቅ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዘበዋል።

በተለይ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ የተፈጥሮ ሀብቷን የማልማትና በፍትሃዊነት የመጠቀም መብት እንዳላት ዓለም አቀፍ መርሆዎችን መሰረት በማድረግ ለዓለም ማህበረሰብ በማሳወቅ ረገድ ምሁራን ግንባር ቀደም ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዘበዋል።

የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ሀብታሙ አበበ በበኩላቸው ትምህርት ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልጽግና መረጋገጥ መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።

ዩኒቨርስቲው የመማር ማስተማር፣ የምርምርና ስርጸት እንዲሁም የማህበራዊ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማጎልበት በ2017 ዓ.ም  በሀገሪቱ ከሚገኙ ምርጥ አስር ዩኒቨርስቲዎች አንዱና የልሂቃን ማመንጫ ለመሆን እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሁለተኛ ዙር ውሀ ሙሌት ለማከናወን በዝግጅት ላይ በምትገኝበት ወቅት ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን ማስመረቁ ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸዋል ።

ተማሪዎች ዋናው አላማቸው መመረቅ ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተግዳሮቶችን በመለየት ችግር ፈቺ ምርምሮችን በማካሄድ ለውጥ ለማምጣት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ መወጣት እንዳለባቸው ፕሬዝዳንቱ አስገንዘበዋል።

በዩኒቨርስቲው በማኔጅመንት ትምህርት ክፍል የማዕረግ ተመራቂ የሆነችው ረድኤት ዘውዴ "ሴቶች ጊዜያችንን በአግባቡ በመጠቀም በርትተን ከሰራን አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ እንችላለን " በማለት የተሰማትን ደስታ ገልጻለች ።

በ2004 ዓ.ም 500 ተማሪዎችን በመቀበል የመማር ማስተማር ስራውን የጀመረው የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት ከ27 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛና በተከታታይ ትምህርት መርሃ ግብር በተለያዩ የትምህርት መስኮች እያስተማረ እንደሚገኝ በስነ ስርአቱ ላይ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም