ምርጫው ሠላማዊ፣ ፍትሓዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየሰራሁ ነው -ብልፅግና ፓርቲ

56

አምቦ፣ ሚያዚያ 30 ቀን 2013 (ኢዜአ) 6ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ሠላማዊ፣ ፍትሓዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየሰራሁ ነው ሲል ብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ።

የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ብልጽግና ሰላም ነው፣ ብልጽግና እውነት ነው፣ ብልጽግናን መምረጥ ልማትና ዴሞክራሲን መምረጥ ነው" የሚሉ መፈክሮችን ይዘው በመውጣት ድጋፋቸውን አሳይተዋል፡፡

ፓርቲው አባላቱና ደጋፊዎቹ በተገኙበት በአምቦ ከተማ በጎዳና ላይ የምርጫ ቅስቀሳ ዛሬ አካሂዷል።

ብልጽግና ፓርቲ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው፤ ብልጽግና በተግባር የተፈተነ ፓርቲ ነው፤ ብልጸግና የኢትዮጵያ ራእይ ነው፤ የሚሉ መፈክሮችም በአባላቱና ደጋፊዎቹ ተላልፈዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የአምቦ ከተማ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሀጫሉ ገመቹ በስነ-ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት ብልጽግና ፓርቲ  6ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ሠላማዊ፣ ፍትሓዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየሰራ ይገኛል፡፡

"ብልፅግናን መምረጥ በሀገሪቱ የተጀመሩ ሁለንተናዊ ለውጦችን አጠናክሮ ማስቀጠል በመሆኑ ህዝቡ ብልጽግናን ይምረጥ" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

"ብልጽግና ፓርቲ የኛ፣ የልጆቻችን፣ ቤተሰባችንና የሀገሪቱ ሁሉ ብርሃን ነው" ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

የአምቦ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራር አቶ ሳህሉ ዲሪብሳ በበኩላቸው ፓርቲው 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሃዊ፣ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና በህዝብ ዘንድ ታዓማኒነት እንዲኖረው የድርሻውን ለመወጣት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ህዝቡ በካርዱ ለሀገር የሚበጀውን የአምፖል ምልክት ያለውን ብልፅግናን እንዲመርጥ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በስነ-ስርዓቱ ከታደሙ መካከል አቶ ቶለሳ ፍቃዱ በሰጡት አስተያየት "ለሀገሪቱ የሚበጀውን ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫ ካርድ የወሰድኩት በመጀመሪያው ቀን ነው" ብለዋል።

ድምጻቸውን ለመስጠት የምርጫውን ቀን በጉጉት እየጠበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"ለሀገር ሰላም፣ አንድነት፣ እድገት፣ ለህዝቦች እኩልነትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለማምጣት የሚበጀኝን ፓርቲ እመርጣለሁ" ብለዋል።

የዘንድሮው ምርጫ ፍትሃዊ፣ ነፃና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የበኩላቸውን እንደሚወጡ የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ አቦነሽ ወልዴ ናቸው፡፡

ብልጽግና ፓርቲ ዛሬ በአምቦ ከተማ ያካሄደው የምረጡኝ ቅስቀሳ አባላትና ደጋፊዎች በተገኙበት "ለኢትዮጵያ ብልጽግና አምፖልን ምረጡ” በሚል መሪ ቃል ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም