የታላቁ የህዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር የውሀ ሙሌት እውን እንዲሆን የድርሻችንን እንወጣለን -የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች

68

ጋምቤላ፣ ሚያዝያ 30/2013 (ኢዜአ) የታላቁ የህዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር የውሀ ሙሌት እውን እንዲሆን የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ድጋፍ  ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።

"የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት የአባይን ውሃ አልምታችህ አትጠቀሙ የሚለው አቋማቸው የጓሮ እሸትህን ቆርጠህ አትብላ እንደማለት ይቆጠራል" ሲሉ ነዋሪዎቹ ለኢዜአ ተናግረዋል ።

ከነዋሪዎቹ መካከል ወጣት ኮንግ ጋድቤል በሰጠው አስተያየት የታላቁ የህዳሴ ግድብ 2ኛው ዙር የውሃ ሙሌት ስኬታማ እንዲሆን የዜግነት ኃላፊነቱን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።

ርካሽ የፓለቲካ ትርፍ ለማግኘት የውስጥ ባንዳዎች የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ከሚቃወሙ ኃይሎች ጋር በማበር የውሃ ሙሌቱን ለማስተጓጎል በሚሞክሩ ኃይሎች ላይ  መንግስት የጀመረውን ህግ የማስከበር ተግባር አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመላክቷል።

መንግስት ለጀመራቸው ህግ የማከበር ስራዎች ስኬታማነት የድርሻውን እንደሚወጣ ተናግሯል።

"ምንም እንኳ የአባይ ወንዝን አልምቶ መጠቀም የማንንም ፍቃድ የማያሻ ቢሆንም መንግስት የጋራ ተጠቃሚነትን እውን ለማድረግ እያካሄደ ያለው ድርድር ተገቢና ታጋሽነትን የሚያሳይ ነው" ያሉት ደግሞ አቶ ኮንግ ጆክ ናቸው።

የኢትዮጵያ መንግስት በጀመረው የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ አንስማማም በማለት ኃይልን ለመጠቀም የሚፈልግ ካለ አስፈላጊውን ሁሉ መሰዋትነት ለመክፋል ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል።

"በተለይም ግብጽ ከኢትዮጵያ አብራክ የመነጨውን የአባይን ውሃ አትጠቀሙም የሚለው አቋሟ የጓሮህን እሸት ቆርጠህ አትብላ እንደማለት ይቆጠራል" ሲሉ አቶ ኮንግ ተናግረዋል።

አቶ አስፋው ገነቴ በበኩላቸው "ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሀብት አልምታ በመጠቀም ከድህነት ለመውጣት የምታደርገውን ጥረት ለማደናቀፍ የሚደረገውን ጥረት ለማክሸፍ በአንድነት መቆም ይገባል" ብለዋል።

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚደረግ ማንኛውንም ጣልቃ ገብነት በመመከት ለግድቡ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌትም ሆነ የግድቡ ግንባታ ፍፃሜውን እስኪያገኝ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉ የገለጹት ደግሞ አቶ ሯች ባይክ ናቸው።

አስተያየት ሰጪዎቹ ለግድቡ ግንባታ በቦንድ ግዥም ሆነ በስጦታ የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

በጋምቤላ ክልል በዘንድሮው በጀት ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 15 ሚሊዮን ብር በቦንድ ሽያጭና በስጦታ ገቢ ለማሰበሳብ እየተሰራ መሆኑን ከክልሉ የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም