በሱዳን በስደት ላይ የነበሩ 138 ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው ተመለሱ

66

መተማ፣  ሚያዚያ 30/2013(ኢዜአ)  በሱዳን በስደት ለበርካታ ዓመታት የኖሩ 138 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን በሱዳን ገዳሪፍ የኢፌዴሪ የቆንስላ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ተወካይ አቶ መሃሪ አንተነህ ለኢዜአ እንደገለጹት ከስደት የተመለሱት ዜጎች ከ15 እስከ 30 ዓመታት በሱዳን ውስጥ በስደት የኖሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ ተችሏል።

በዚህም አሜሪካ ከሚገኘው ግፉሃን ማህበር፣ ከሱዳን ፖሊስ፣ ኢሚግሬሽን፣ ጉምሩክ እና መረጃ ደህንነት መስሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር ስደተኞቹ በሰላም ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን ገልጸዋል።

ሱዳን ውስጥ በተፈጠረው የኑሮ ውድነትና ሌሎች ችግሮች ምክንያት ከሁለት ዓመታት በፊት ጀምሮ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ወደ ሀገራቸው እየተመለሱ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም በርካታ ኢትዮጵያዊያን በስደት በሚኖሩባት የገዳሪፍ ግዛት የሚኖሩ ስደተኞችን ወደ ሃገራቸው ለመመለስ የቆንስላ ጽህፈት ቤቱ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

“በምዕራብ ጎንደር ዞን አመራሮች እና የመተማ ዮሐንስ ከተማ ማህበረሰብም ከስደት ለተመለሱ ወገኖች የምግብ፣ የመጠጥና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ አጋርነቱን እያሳየ ነው” ብለዋል።

የመተማ ዮሃንስ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አንዳርግ ሞላ በበኩላቸው ዛሬ የመጡትን ስደተኞች ጨምሮ 338 ከስደት ተመላሾች በከተማዋ ይገኛሉ።

ከከተማ አስተዳደሩና ከዞኑ ምግብ ዋስትናና አደጋ መከላከል መስሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር አስፈላጊው ድጋፍ መደረጉን ጠቁመው “በቀጣይም ተመላሾችን በቋሚ የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው” ብለዋል።

ከተመላሾች መካከል አቶ አንጋው ደብልል በስደት ለ16 ዓመታት ከኖሩበት ሱዳን ወደ ሃገራቸው መመለሳቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸው መንግስት የተለያዩ ድጋፎችን እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው በሀገራቸው ሰርተው በመለወጥ ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውን ከመጥቀም ባሻገር በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

ሌላኛው ከስደት ተመላሽ አቶ አወቀ አቸነፍ በህወሃት አገዛዝ ስርአት ሲደርስባቸው ከነበረው ተፅዕኖ ለመላቀቅ ከ28 አመታት በላይ ለስደት መዳረጋቸውን ገልፀዋል።

በቀጣይ በሀገራቸው ሰርተው ለመለወጥ እና በሀገር እድገት ግንባታ የበኩላቸውን ለመወጣት እንደሚሰሩ በመግለጽ ወደ ሀገራቸው በሰላም እንዲመለሱ ላደረጉ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም