የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ በዘጠኝ ወራት 6 ሚለዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

74

ሚያዚያ 30 /2013 (ኢዜአ) የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ወደ ውጭ ከላካቸው ልዩ ልዩ ምርቶች 6 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ።

የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ መስከረም 27 ቀን 2011 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ስራ መጀመሩ ይታወሳል።

የኢንዱስትሪ ፓርኩ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ደርቤ ደበሌ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ፓርኩ ባለፋት 9 ወራት ወደ ውጭ ከላካቸው የተለያዩ ምርቶች 6 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ አግኝቷል።

የኮሮናቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ ስራው ላይ ከፍተኛ ጫና እንዳስከተለ ጠቅሰው አገሪቷ ከውጭ ምንዛሬ ማግኘት ያለባትን ገቢ  እንዳታጣና ፓርኩ ገቢው እንዳይቋረጥ ጥረት መደረጉን አስታውሰዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ብቻ ወደ ውጭ ከላካቸው ልዩ ልዩ ምርቶች 6 ሚለዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን ገልጸዋል።

ፓርኩ የውጭ ምንዛሬ ከማስገኘቱ በተጨማሪ በስራ እድል ፈጠራና በቴክኖሎጂ ሽግግር ጉልህ አስተዋፆ ማበርከቱንም ተናግረዋል።

በፓርኩ ውስጥ ከሚገኙት 19 የመሥሪያ ሼዶች ሁሉም በአልሚዎች የተያዙ ሲሆን ከእነዚህ ወስጥ 12ቱ የተለያዩ ምርቶችን በማምረት ላይ መሆናቸውን አቶ ደርቤ ገልጸዋል።

የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ አሁን ላይ ለ7 ሺህ ዜጎች የስራ እድል ያስገኘ ሲሆን ከነዚህም መካከል መሬታቸውን ለልማት አሳልፈው የሰጡ 360 አርሶ አደሮች ስራ ተሰጥቷቸዋል ብለዋል።

ፓርኩ በአካባቢው ላለው ማህበረሰብ ማህበራዊ አገልግሎት አስተዋጾ በማድረግና ለዜጎች የስራ እድል የመፍጠር እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ የማስገኘት ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ በምርት ሂደት ላይ ከሚገኙት መካከል በአሥር ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተገነባው የቻይናው የጨርቃ ጨርቅ አምራች ኩባንያ አንዱ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም